አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዘጠኝ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኢትዮጵያን ወክለው በ7ኛው የሁዋዌ ዓለም አቀፍ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጅ (አይ ሲ ቲ) ፍጻሜ ውድድር ለመሳተፍ ቻይና ገብተዋል፡፡
ሁዋዌ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ፥ ውድድሩ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ግንቦት 20 ቀን 2015 ዓ.ም በቻይና ሼንዘን ከተማ ይካሄዳል፡፡
በዚህ ውድድር ላይ የሚሳተፉት ተማሪዎች የተለያዩ ሀገር አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ውድድሮች ላይ ተሳትፈው በየደረጃው በአሸናፊነት ያጠናቀቁ መሆናቸው ታውቋል።
ከጉዟቸው በፊት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እና የምናብ አይ ሲ ቲ ሶሉሽንስ እና ሃሁ ጆብስ ዋና ስራ አስፈፃሚ እና መስራች ቃለአብ መዝገቡ በተገኙበት የማበረታቻ የሽኝት ስነ ስርዓት ተካሂዷል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ለወጣት ተማሪዎች ዓለም አቀፍ ልምድ ማግኘት አነቃቂና አበረታች መሆኑን ጠቅሰው፥ “ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ ስለወከላችሁ ልትኮሩና በማሸነፍም የህዝብ ኩራት እንደምትሆኑ አምናለሁ” ብለዋል፡፡
አቶ ቃለአብ በበኩላቸው ሁዋዌ እድሉን በመፍጠሩ አመስግነው በውድድሩ ዓለም አቀፉን የአይ ሲ ቲ ሥነ ምህዳር ለመገንዘብና ለተተኪዎቻቸው ምሳሌ ለመሆን እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
የሁዋዌ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሊሚንግ ዬ ድርጅቱ በቀጣይም በኢትዮጵያ ትምህርት ላይ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ዘርግቶ የሚያደርገውን እገዛና ቁርጠኝነት እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።
ዘጠኙ ተማሪዎች የተገኙት ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ዋቸሞ፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች መሆኑ ተጠቁሟል።
ተማሪዎቹ እያንዳንዳቸው ሶስት አባላት ያላቸው ሶስት ቡድን ያላቸው ሲሆን “በፕራክቲካል ትራክ (ዳታኮም፣ ሴኪዩሪቲ፣ WLAN፣ ቢግ ዳታ፣ ስቶሬጅ፣ AI፣ OpenEuler እና OpenGaussን ያካትታል) ሁለት ቡድን እና አንድ ቡድን በኢኖቬሽን ትራክ ይሳተፋሉ ተብሏል።
በኢኖቬሽን ትራክ የሚወዳደሩት ተማሪዎች የራሳቸውን የፈጠራ ሃሳብ ይዘው የሚቀርቡ ሲሆን ተማሪዎቹ “የግእዝ ፊደላት ክላሲፋየር” የተሰኘ ውድድር ይዘው መቅረባቸውንም መግለጫው አመላክቷል።