የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያ በቤት ለቤት ቅኝት ከ3 ሚሊየን በላይ ቤቶች ተዳርሰዋል – ዶክተር ሊያ

By Tibebu Kebede

April 24, 2020

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሃገር አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በተካሄደው የቤት ለቤት ቅኝት ከ3 ሚሊየን በላይ ቤቶች መዳረሳቸውን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

ሚኒስትሯ እንደገለፁት በሃገሪቱ እየተካሄደ ባለው የቅኝት ሥራ ዳሰሳው ተካሂዷል።

ቅኝቱ የቫይረሱ ስርጭት በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ ያስችላል ብለዋል።

በዚህም የቫይረሱ ምልክት የታየባቸው 427 የሚሆኑ ሰዎች መለየታቸውን ተናግረዋል።

ቫይረሱን ለመከላከል እየተካሄደ ባለው እንቅስቃሴ መጀመሪያ ትኩረት የተደረገው በአውሮፕላን ማረፊያዎችና በየብስ በሚገቡ ሰዎች ላይ መሆኑን አስታውሰው፥ በሂደት ዳሰሳው በአዲስ አበባና በክልሎች እንዲስፋፋ መደረጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ጣቢያዎችን የማደራጀቱ ሥራ መጠናከሩን አንስተዋል።

በዚህም በአሁኑ ወቅት የጣቢያዎቹ ቁጥር 20 መድረሳቸውንና የመመርመር አቅማቸው እያደገ መምጣቱን ኢዜአ ዘግቧል።

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።