ዓለምአቀፋዊ ዜና

አንቶኒዮ ጉተሬዝ ዓለም ለሁለት እንዳትከፈል ሲሉ አስጠነቀቁ

By Tamrat Bishaw

May 21, 2023

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ዓለም ለሁለት እንዳትከፈል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

የቡድን 7 አባል አገራት ከአሜሪካ ወይም ከቻይና ጋር በመሰለፍ ዓለምን በቀዝቃዛ ጦርነት ጎራዎች ከመከፋፈል እንዲቆጠቡ ዋና ፀሐፊው አሳስበዋል።

የምዕራቡ ዓለም መሪዎች በሩሲያ እና ቻይና የኒውክሌር ጦር መሳሪያን አስመልክቶ በሰጡት የጋራ መግለጫ ላይ ትኩረታቸውን እንዳደረጉ የአር ቲ ዘገባ አመላክቷል፡፡

ሩሲያ እና ቻይና በቅርቡ ሁሉም አገራት የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ከግዛታቸው ውጭ ማስቀመጥ እንደማይገባቸው እና ውጭ የተቀመጡትን የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎቻቸውንም በሙሉ ማንሳት አለባቸው ሲሉ በመግለጫቸው አጽንዖት መስጠታቸው ተመላክቷል።

የካናዳ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የጣሊያን፣ የጃፓን፣ የእንግሊዝ እና የአሜሪካ መሪዎች ቅዳሜ በሂሮሺማ ተገናኝተዋል፡፡

ጉተሬዝ በቡድን 7 አባል አገራት እና በቻይና በአየር ንብረት ጉዳዮች ላይ ንቁ ውይይት እና ትብብር እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ዋና ፀሐፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በምዕራቡ ዓለም እና በቻይና መካከል ያለው ግንኙነት ለከት ሊኖረው እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዓለምን ለሁለት የሚከፍል እንቅስቃሴን በማስወገድ ተገቢ ውይይቶችን ለማካሄድ ድልድይ መፍጠሩ ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ፅኑ እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

ጉተሬዝ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በምዕራባውያን አገሮች እና በቻይና መካከል የቀዝቃዛ ጦርነት እንደሚቀሰቀስ ደጋግመው ሲያስጠነቅቁ መቆየታቸውን ዘገባው አያይዞ ገልጿል፡፡

በ2019 የሁለቱም ወገኖች ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ጥቅሞች ወደ ተለያየ አቅጣጫ ያዘነበለ ሲሆን ዋና ፀሐፊው ሁኔታውን “ታላቅ ስብራት” ሲሉ መጥራታቸው የሚታወስ ነው።