የሀገር ውስጥ ዜና

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ዘንድሮ የሚተከሉ ችግኞች ያሉበትን ደረጃ ጎበኙ

By Tibebu Kebede

April 24, 2020

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 16 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዘንድሮው አመት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚተከሉ ችግኞች ዝግጅት ያሉበትን ደረጃ ጎብኙ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያ ክልል ሶደሬ አካባቢ በመገኘት ነው የችግኝ ማፍላት ስራውን ከክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጋር በመሆን የጎበኙት።

በዘንድሮው አመት 5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ለዚህም የሚሆን ችግኝ የማዘጋጀት ስራ በሀገር አቀፍ ደረጃ በ3 ሺህ 800 የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች እየተካሄደ እንደሚገኝ መግለፃቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

አብዛኛዎቹ ችግኞችም ለምግብነት የሚውሉ እንደ አቮካዶ እና ማንጎ ያሉ የፍራፍሬ ተክሎች ናቸው።

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን መግታት ከተቻለ ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ ችግኞቹን መትከል እንደሚጀመርም ገልጸዋል።

ባለፈው አመት 4 ቢሊየን ችግኝ በሀገር አቀፍ ደረጃ መተከሉን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የዝናቡ ሁኔታ ጥሩ ስለነበረ እና እንክብካቤ በመደረጉ ምክንያት አብዛኛዎቹ መጽደቅ መቻላቸውን እንደገለፁ ነው ዘገባው የጠቆመው።

የዘንድሮውን ጨምሮ በቀጣይ 4 አመታት እስከ 20 ቢሊየን ችግኞችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመትከል እየተስራ መሆኑንም ጠቅላይሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ይህም ሀገራዊ የደን ሽፋንን በማሳደግ የተሻለ የዝናብ መጠን ለማግኘት ያስችላልም ነው ያሉት።