የሀገር ውስጥ ዜና

በአቶ አገኘሁ ተሻገር የተመራው ልኡክ የሩሲያ የሥራ ጉብኝቱን ቀጥሏል

By Alemayehu Geremew

May 18, 2023

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢ.ፌ.ዲ.ሪ.የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር የተመራው ልኡክ በሩሲያ የሚያደርገው የሥራ ጉብኝት ቀጥሏል፡፡

ልዑካን ቡድኑ ረቡዕ ዕለት ግንቦት 9 ከሰዓት በኋላና ሐሙስ ግንቦት 10 ቀን 2015 ከተለያዩ የሩሲያ መንግስት አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ቦግዳኖቭ ጋር በነበራቸው ቆይታ ÷ በቅርቡ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው በ2ኛው የሩሲያ-አፍሪካ ፎረም ላይ በተለያዩ ጉዳዮች መክረዋል፡፡

ከመከሩባቸው ነጥቦች መካከል በተፈረሙ ሥምምነቶች አተገባበር፣ በነጻ የትምህርት ዕድል፣ ከህወሐት ጋር በተደረሰው የሠላም ሥምምነት፣ በሐይማኖት ተቋማት እና በገዢ ፓርቲዎች መካከል ባለው ግንኙነት ይጠቀሳሉ፡፡

በተጨማሪም የአፍሪካ ሕብረት መርኅ በሆነው “ለአፍሪካን ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” ሐሳብ ላይ እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች ላይ ያጠነጠኑ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ የሥራ ቋንቋዎች መካከል ከሆነው አማርኛ ቋንቋን ጨምሮ በ54 የተለያዩ የዓለም ቋንቋዎች በማስተማር በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ከተመዘገበው በሞስኮ የሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎች ጋርም ተወያይተዋል፡፡

በቅርቡ የመግባቢያ ሰነድ ከተፈራረሙት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ ከሌሎች የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር መስራት በሚችሉበት ማዕቀፍ ላይም መወያየታቸው ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ተማሪዎች በሩሲያ ነጻ የትምህርት ዕድል ማግኘት በሚችሉበት ሁኔታ ላይም መክረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የአማርኛ ቋንቋ ተማሪዎች በሁለቱ ሀገራት ግንኙነትና ትብብር ዙሪያ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ከሩሲያ ፌዴሬሽን የኢነርጂ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ሞቻልክኮቭ ሰርጌይ ጋር በነበራቸው ውይይት ሁለቱ ሀገራት በኃይል፣ ሥነ-ምድር እና በሌሎች ዘርፎች በጋራ ለመሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡