አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዶኔዥያዋ ዋና ከተማ ጃካርታ በዓለም በህዝብ ብዛቷ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ኢንዶኔዥያ ነፃ በወጣችበት በፈረንጆቹ 1945 ጃካርታ ከ1 ሚሊየን ያነሰ የሕዝብ ቁጥር የነበራት ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ይህ አሃዝ በእጅጉ ማደጉ ይነገራል፡፡
ኢንዶኔዥያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጎሳዎች ያሏትና በዛው ልክ ቋንቋዎች የሚነገሩባት ሃገር እንደሆነች መረጃዎች ያመላክታሉ።
ጓዳዋን ልቃኝ ብሎ እግሩ ለረገጠ መንፈስን የሚያድስ ተፈጥሮ፣ የተለየየ የባህል ስብጥር፣ የበለጸገ ታሪክን የሚቋደሱበት፣ የተለያዩ ባህላዊ ምግቦችን የሚያጣጥሙባት እና ቀን ከሌት ለመድመቅ የማይሰንፉ የገበያ ማዕከላት መገኛም ናት – ጃካርታ፡፡
ሆኖም በከተማዋ ጥቅጥቅ ብለው የሚታዩ የህንጻ ጫካ ያላትና በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት ውበቷን እንደልብ ለመጎብኘት የሚያስችል እንዳልሆነ የሚያነሱ ብዙዎች ናቸው፡፡
በተመሳሳይም የተበከለ አየር የከተማዋ መገለጫ ከመሆኑ የተነሳ በተደጋጋሚ የዓየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ ከሚመጡ አደጋዎች ጋር ስሟ አብሮ ይነሳል፡፡
ከዓየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ለሚከሰተው የጤና ቀውስ ሚሊየን ዶላሮችን ፈሰስ እንደምታደርግም ነው የሚገለጸው፡፡
በአሁኑ ወቅትም 10 ሚሊየን ህዝብ በውስጧ የያዘችው ከተማ እየሰጠመች እንደምትገኝ ተሰምቷል፡፡
የዚህ መንስዔው ከዓየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚያያዝ እንደሆነ ነው ኒውዮርክ ታይምስ ያወጣው ዘገባ የሚያመላክተው።
የደን መጨፍጨፍ፣ የተጨናነቀ ከባቢ እና የከተማ ፍሳሽ ማስወገጃዎች ለዚህ ችግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋልም ነው የተባለው፡፡
በዚህም 40 በመቶው የከተማዋ ክፍል ከባህር ወለል በታች ይገኛል ተብሏል፡፡
በተደጋጋሚ ኢንዶኔዢያን የሚያጠቃት የጎርፍ አደጋ እና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ችግር በመገንዘብ ችግሩን ለመቅረፍ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆኮ ዊዶዶ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ እንደነበርም ዘገባው አትቷል፡፡
ሆኖም ይህ ጥረታቸው ግን ጃካርታን ማዳን ሳይችል እንደቀረም ነው የተነገረው፡፡
በዚህም ጃካርታ እየሰጠመች ስለሆነ መፍትሄ ፍለጋ እየባዘኑ ሲሆን ፥ በዓለም ሦስተኛዋ ትልቅ ደሴት ከሆነችው ቦርኒዮ ላይ አዲስ ከተማ ለመገንባት እየተንቀሳቀሱ ነው ተብሏል፡፡
አዲሱ ዋና ከተማ ኑሳንታራ ተብሎ ሊጠራ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
ፕሬዚዳንቱ ምኞታቸው የጃካርታን ነዋሪዎች ከማትረፍ የዘለለ ነው ተብሏል ፤ ኑሳንትራ ትራፊክ መጨናነቅ የማይታይባት፣ ሰዎች በብስክሌት የሚንሸራሸሩባት የቴክኖሎጂ ከተማ ትሆናለችም ነው ያሉት፡፡
አዲሷን ኢንዶኔዢያ መገንባት እንፈልጋለን ያሉት ፕሬዚዳንቱ ፥ በህንጻ ሳይሆን አዲስ የስራ ባህል፣ አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመፍጠር እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ እየሰጠመች ያለችው ጃካርታን መታደግ ካልተቻለ የጎብኚዎች መናኸሪያዋ ከተማ በሚቀጥለው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ዋና ከተማነቷን ልታስረክብ ትችላለች ነው የተባለው።
ያ ከመሆኑ በፊት አሁንም ማንኛውንም አይነት ጥረት እናደርጋለን ነው የሚሉት የቀድሞው የከተማ ገዢ የአሁኑ ፕሬዚዳንት ጆኮ ዊዶዶ።