አዲስ አበበ ፣ ግንቦት 8 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና የኮሪያ ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) የ10 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ።
የድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው እና በኢትዮጵያ የኮይካ ሃላፊ ሊ ቢዩንግህዋ ተፈራርመውታል።
ድጋፉ በኢትዮጵያ የወተት እና የወተት ተዋጽኦ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ሲሆን፥ ፕሮጄክቱም ለቀጣዮቹ ስድስት አመታት እንደሚተገበር የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
ፕሮጄክቱ ዕሴት በመጨመር በዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን፥ በዘርፉ ያለውን አሰራር እንደሚያዘምንም ታምኖበታል።
በዚህም የተሻሻሉ የወተት ላሞችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ የወተት ምርታማነትን መጨመር፣ በማህበር የተደራጁ ወተት አቅራቢዎችን የገበያ ተሳትፎ ማሳደግ እና የዘርፉን ኢንዱስትሪ ልማት ማሳደግ የሚያስቸሉ ዘመናዊ አሰራሮችን መተግበር የፕሮጄክቱ አላማ መሆኑም ታውቋል።