የሀገር ውስጥ ዜና

የኔዘርላንድሱ “ቪኦን.ቴሌኮም” በኢትዮጵያ እንዲሠራ ጥሪ ቀረበለት

By Alemayehu Geremew

May 16, 2023

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኔዘርላንድሱ “ቪኦን.ቴሌኮም” በኢትዮጵያ እንዲሠራ ጥሪ ቀረበለት፡፡

የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከ“ቪኦን.ቴሌኮም” ግሩፕ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ማቲው ጋልቫኒ ጋር በበይነ-መረብ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱም የቪ ኦን ቴሌኮምን ጥልቅ የሥራ ልምድ በማድነቅ ኩባንያው ልምዱን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ቢሰራ ውጤታማ እንደሚሆንም ገልጸውላቸዋል፡፡

የ“ቪኦን. ቴሌኮም” ግሩፕ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ማቲው ጋልቫኒ በበኩላቸው ÷ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሐብት ለማሳደግ እየሠፋ በመጣው የሥራ ዕድል መደነቃቸውን ገልጸዋል፡፡

የ“ቪኦን”ን የገበያ ዕድል እና አማራጮች የማሥፊያ ሥልቶችንም ከልምዳቸው አካፍለዋል፡፡

ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የ“ቪኦን.ቴሌኮም” ግሩፕ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ማቲው ጋልቫኒ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ እና ያሉትን የቢዝነስ አማራጮች በአካል እንዲቃኙ ጋብዘዋል፡፡

ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ በቴሌኮሙኒኬሽኑ ዘርፍ በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን ማፍሰስ ከሚፈልጉ አካላት ጋር ለመሥራት ግንኙነቱን መቀጠሉን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡