የባንኩ የኮርፖሬት ኮሙኑኬሽን ዳይሬክተር አቶ አልሰን አሰፋ እንዳስታወቁት÷ ባንኩ ዘመናዊ፤ለአጠቃቀም ቀላልና ፈጣን የሆነውን የሲ ቢ ኢ ብር አገልግሎትን ከግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም.ጀምሮ በሁሉም አካባቢዎች በሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ተግባራዊ ያደርጋል።
ከሚያዚያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ በተጀመረው በዚሁ አገልግሎት መልካም ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው፥ በርካታ ደንበኞች የሲ ቢ ኢ ብር የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ዘዴን በእጅ ስልኮቻቸው ላይ በመጠቀም ነዳጅ ተገበያይተዋል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የተገኘውን ልምድ መሰረት በማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከነገ ጀምሮ ለሚተገበረው የኤሌክትሮኒክ የነዳጅ ግብይት ሙሉ ዝግጅቱን ባንኩ ማጠናቀቁንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ደንበኞች ነዳጅ ለመቅዳት የሲ ቢ ኢ ብር መተግበሪያን በእጅ ስልኮቻቸው ላይ ጭነው *847# ላይ በመደወል አገልግሎቱን መጠቀም እንደሚችሉም ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም ለዚሁ አገልግሎት ባንኩ ያበለጸገውን “ነዳጅ” የተሰኘ የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያን በመጫን ሊጠቀሙ ይችላሉ ተብሏል፡፡
ሁሉንም መተግበሪያዎች ደንበኞች በነጻ ከአፕ ስቶር፣ ፕለይ ስቶር፣ እና ጎግል ፕለይ ከተሰኙ ድረ-ገጾች ላይ ማውረድ እና መጫን የሚቻሉ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
የባንኩ ባለሙያዎችም በሁሉም የነዳጅ ማደያዎች በመገኘት ለደንበኞችና ለነዳጅ ማደያ ሰራተኞች አስፈላጊውን እገዛ ስለሚሰጡ ደንበኞች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉላቸውም ጠይቀዋል፡፡