የሀገር ውስጥ ዜና

ሀገር በፈተናዎች ውሥጥ ሆና ያከናወነቻቸው ፕሮጀክቶች በአግባቡ ሊሰነዱ እንደሚገባ ተመለከተ

By Amele Demsew

May 05, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገር በፈተናዎች ውሥጥ ሆና ያከናወነቻቸው ፕሮጀክቶች በአግባቡ ሊሰነዱና በቀጣይ ፕሮጀክቶች መማሪያ ሊሆኑ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

አራተኛውን ቀን በያዘው በአብርሆት ቤተ መጻሕፍት “ቃል፤ ተግባር፤ ትውልድ” በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ በሚገኘው የመጽሐፍ ዐውደ ርዕይ ”ከመጋቢት እስከ መጋቢት” በተሰኙት ከ2010-2013 የተከወኑ ሀገራዊ ሂደቶችን በሚዳሥሡ ሶሥት ተከታታይ መጻህፍት ላይ ውይይት ተደርጓል።

በመጻህፍት ዳሰሳው ላይ የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ ፥ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አሥኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ እና አርሶ አደር አሸናፊ አያሌው በመጻህፉቱ ዙሪያ ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

በውይይቱም ፥ ኢትዮጵያ ፕሮጀክቶችን በመፈጸም ረገድ ያገኘቻቸው ሥኬቶችና የገጠሟት ፈተናዎች በመጻህፍቱ መነሻነት መዳሰሳቸውን ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተጨማሪም፥ የተገነቡ ፕሮጀክቶች አሥቀድሞ ግብን ከመተለም አንስቶ ለሥኬት እውን መሆን በቁርጠኝነት መሥራትን ያሥተማሩ መሆናቸው ተነሥቷል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ አመንጭነት በተከናወኑ ፕሮጀክቶችም ሆነ በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥብቅ ክትትል መደረጉ ለውጤቱ መነሻ እንደሆነም ተጠቁሟል።

ሀገር በበርካታ ፈተናዎች ውሥጥ ሆና ያሳካቻቸውና የከወነቻቸው ፕሮጀክቶች በአግባቡ ሊሰነዱና በቀጣይ ፕሮጀክቶች መማሪያ ሊሆኑ እንደሚገባም በውይይቱ ተመላክቷል።