አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍርድ ቤቱ መስከረም አበራን ጨምሮ ስድስት ግለሰቦች በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል መዝገብ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ፖሊስ ያቀረበውን የሽብር ወንጀል የጥርጣሬ መነሻን እና የተጠርጣሪዎችን የመከራከሪያ ነጥብ ተመልክቶ ነው ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀን የፈቀደው።
በሽብር ወንጀል ተጠርጠረው ዛሬ ከሰዓት ፍርድ ቤት የቀረቡ ተጠርጣሪዎችም መስከረም አበራ፣ ሳሮን ቀባው፣ ዮርዳኖስ አለሜ፣ ቢሰጥ ተረፈ፣ አሰፋ አዳነ (ዶ/ር) እና ታደሰ መንግስቱ ይባላሉ።
ተጠርጣሪዎቹ ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስ በማሰብ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት በመፍጠር፣ ወጣቶችን በመመልመል፣ ለሽብር ወንጀል የሚውል ገቢ በማሰባሰብ ተግባር ተሳትፈዋል ሲል መርማሪ ፖሊስ የጥርጣሬ መነሻውን በዝርዝር ጠቅሶ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አቅርቧል።
በዚህ የሽብር ወንጀል የመነሻ ጥርጣሬ ተጨማሪ ማስረጃ ሰብስቦ ለመቅረብ 14 ቀን እንዲሰጠው ጠይቋል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ÷ ሁሉም ተጠርጣሪዎች ከዚህ በፊት በሌላ ፍርድ ቤት በሁከትና ብጥብጥ ማስነሳት ወንጀል ተጠርጥረው በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ እየቀረቡ ባለበት ሂደት ላይ ዛሬ የሽብር ወንጀል ተብሎ መቅረባቸው ተገቢነት የለውም ሲሉ ተከራክረዋል።
ስለሆነም የተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብት እንዲከበር ጠይቀዋል።
መርማሪ ፖሊስም ከዚህ በፊት በተጠረጠሩበት ሁከትና ብጥብጥ አመጽ ማስነሳት ወንጀል ላይ በተደረገባቸው የማጣሪያ ምርመራ የሽብር ወንጀል መፈፀሙን የሚያመላክቱ ተጨማሪ ማስረጃዎች በመገኘታቸው ምክንያት በሽብር ወንጀል መዝገብ እንዲቀርቡ ማድረጉን ጠቅሶ መልስ ሰጥቷል።
ዛሬ ከሰዓት የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡን የተመለከተው ችሎቱ ተጨማሪ ምርመራ መደረጉ አስፈላጊ ነው በማለት ለፖሊስ የ14 ቀን ጊዜ ፈቅዷል።
በታሪክ አዱኛ