አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በለውጡ ማግስት የነበሩ አበይት ሁነቶችን ሰንዶ የያዘው እና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተዘጋጀው “የለውጥ ጎዳና” የተሰኘ መጽሐፍ ለተመራማሪዎች ጠቃሚ ግብዓት ሆኖ ማገልገል እንደሚችል ተመለከተ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተዘጋጀው ዐውደ ርዕይ ሁለተኛ ቀን ዛሬም ቀጥሎ ውሏል።
በዛሬው ውሎም በጽሕፈት ቤቱ የተዘጋጀ የለውጥ ጎዳና የተሰኘ መጽሐፍ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
መጽሐፉ ከየካቲት 6 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጳጉሜን 6 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የነበሩ ዋና ዋና ሁነቶችን ያካተተ ነው።
ይህ መጽሐፍ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁነቶች በተጨማሪ በዓመቱ የተካሄዱ ዋና ዋና ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁነቶችንም መዝግቧል፡፡
መጽሐፉ በሀገራዊ ለውጡ የመጀመሪያ ጊዜያት የነበሩ ሁነቶችን በተገቢው መልኩ በመሰነድ፣ ኢትዮጵያ ያለፈችበትን የለውጥ መንገድ፣ የተመዘገቡ ስኬቶችንና ያጋጠሙ ፈተናዎችን መለስ ብሎ የሚያስቃኝ መሆኑም ተነሥቷል።
በውይይቱ ላይ ሐሳብ የሰጡት የታሪክ ባለሙያው ታምራት ኃይሌ (ዶ/ር)፥ በኢትዮጵያ ታሪክ የነገስታቱን የየዕለት ውሎ የሚመዘግብ ዜና መዋዕል እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡
በዚህ መጽሐፍም ከ570 በላይ በሆኑ ቀናት የተደረጉ ሁነቶች መመዝገባቸውን አስረድተዋል፡፡
መጽሐፉ ከዜና መዋዕል በተለየ መልኩ ገለልተኛ በሆነ ሁኔታ ደረቅ እውነት ብቻ የተመዘገበበት ስለመሆኑም ነው የገለጹት፡፡
የተመዘገቡትን ሁነቶች በመመርመርም በኢትዮጵያ የተደረገው ለውጥ ሪፎርም መሆኑን መግለጽ ይቻላል ብለዋል፡፡
በመሆኑም መጽሐፉ ለታሪክ ባለሙያዎች፣ ለጋዜጠኞች እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የነበረውን ሁነት በአግባቡ የሚገልጽ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
የመጽሐፍ ዐውደ ርዕዩ በነገው ዕለትም የሚቀጥል ይሆናል።
በዘመን በየነ