አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ናይጄሪያ የኢትዮጵያን የስንዴ ምርታማነት ልምድ መጋራት እንደምትፈልግ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት ካሺም ሼቲማ ገልጸዋል።
በናይጄሪያ አዲሱ ተመራጭ ምክትል ፕሬዚዳንት ካሺም ሼቲማ የተመራው ከፍተኛ ልዑክ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገውን የስንዴ ምርታማነት ተሞክሮ ለመውሰድ የሚያስችል ውይይት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር አድርጓል።
የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት ካሺም ሼቲማ እንደተናገሩት÷ የኢትዮጵያ የስንዴ ልማት ተሞክሮ ለሌሎችም ሀገራት መወሰድ አለበት፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት ስንዴ ከውጭ ስታስገባ የነበረችው ኢትዮጵያ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት የስንዴ ምርት ፍጆታዋን በሀገር ውስጥ ከመሸፈን አልፋ ለውጭ ገበያ ማቅረቧ የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም በዓመት 2 ቢሊየን ዶላር ስንዴን ከውጭ ለማስገባት ወጪ የምታደርገው ናይጀሪያ የስንዴ ምርታማነትን መጨመር የምትችልባቸውን መንገዶች ከኢትዮጵያ መማር ትፈልጋለች ነው ያሉት ።
ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ልማት ያስመዘገበችው ስኬት ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በማደግ ላይ ላሉ የዓለም ሀገራትም ምርጥ ተሞክሮ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ ( ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ ካስመዘገበቻቸው ለውጦች ልምድ ለመውሰድ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ስኬትን ለማስመዝገብ ያለፈችባቸውን ሂደቶች ለሌሎች በማካፈል ድጋፍ ለማድረግም ዝግጁ መሆኗን ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።