አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል የቤት ለቤት የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት ዘመቻ መጀመሩን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል።
የቢሮው ሃላፊ አቶ ሮት ጋትዊች እንዳሉት÷ የቤት ለቤት የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት የወባ በሽታን ለመከላከል በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለ20 ተከታታይ ቀናት ይተገበራል።
በዘመቻው ከ130 ሺህ በላይ ቤቶች የፀረ ወባ ኬሚካል ለመርጨት መታቀዱን ነው አቶ ሮት የተናገሩት።
ህብረተሰቡ የፀረ ወባ ኬሚካል በሰው ላይ ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንደሌለው ተገንዝቦ÷ መኖሪያ ቤቱንና አካባቢውን የፀረ ወባ ኬሚካል በማስረጨት ራሱንና ቤተሰቡን ከወባ በሽታ እንዲከላከል አሳስበዋል።
የወባ በሽታን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የተለያዩ አጋር ድርጅቶች እየተሳተፉ እንደሚገኙም የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት መረጃ ያመላክታል፡፡
ነዋሪዎች የሰለጠኑ የወባ ርጭት ባለሙያዎች በሚመጡበት ወቅት ምግብና የምግብ ቁሳቁሶችን ከቤት በማስወጣትና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡