Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ፍርድ ቤቱ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ ነበር ተብለው በተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች ላይ የ9 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍርድ ቤቱ ሕገ-መግስቱን እና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ ነበር ተብለው በተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች ላይ የዘጠኝ ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ፈቅዷል።
 
የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲከናወንባቸው ተጨማሪ ጊዜ የፈቀደው ፖሊስ የሰራውን ምርመራ ከተመለከተ በኋላ ነው፡፡
 
ለተጨማሪ ምርመራ የጊዜ ቀጠሮ የተፈቀደባቸው ተጠርጣሪዎችም ጌታሆይ አለሙ ተበጀ፣ ሃብታሙ ዳኜ ፣ዳዊት አባቡ፣ ቴድሮስ ተሾመ፣ ጌታቸው ጥዑመ ልሳን ፣ትዛዙ ታረቀኝ፣ ሙሉቀን ወንዴ፣ ዋና ሳጅን ቢያዝን ምህረቱ፣ ምስጋና ማሩ፣ በቀለ ሃይሌ (ዶ/ር) እና ጌትነት ወንደሰን ናቸው።
 
ፖሊስ በጀመረው የምርመራ ስራ ተጠርጣሪዎቹ ኢ -መደበኛ መዋቅራዊ አደረጃጀት ፈጥረው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ማስረጃ ሰብስበናል ሲል ለችሎቱ አብራርቷል።
 
ለወንጀል ተሳትፏቸው የሚያስረዱ የምስክሮችን ቃል መቀበሉን እና በእጃቸው ላይ የተገኙ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን በሚመለከተው አካል እንዲመረመር መላኩንም አስረድቷል።
 
የገንዘብ ዝውውርን በሚመለከት ለማጣራት ለባንኮች ማስረጃ መጠየቁንም ነው ፖሊስ ለችሎቱ ያብራራው።
 
ተጨማሪ የምስክር ቃል ለመቀበል እና ቀሪ ስራዎችን አከናውኖ ለማቅረብም የ14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።
 
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆችም ለፖሊስ ከዚህ በፊት የተሰጠው ጊዜ በቂ መሆኑን ጠቅሰው÷ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ሊሰጥ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
 
የተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብት እንዲፈቀድም ጠይቀዋል።
 
መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ÷ ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ ምስክር ሊያስፈራሩና ሊደልሉብን እንዲሁም በመንግስት የተጀመረውን የሕግ ማስከበር ስራ ሊያደናቅፉ ይችላሉ ሲል ስጋቱን ገልጾ የዋስትና ጥያቄያቸውን ተቃውሟል።
 
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የፖሊስን የምርመራ መዝገብ አስቀርቦ ከተመለከተ በኋላ የቴክኒክና የፎረንሲክ ማስረጃዎች መሰብሰባቸውን መመልከቱን አብራርቷል።
 
በዚህ መሰረትም ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹ የጠየቁትን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው ውድቅ በማድረግ ለተጨማሪ ምርመራ ለፖሊስ የ9 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።
 
በዚሁ መዝገብ ተካታ የነበረችው ሳሮን ቀባው የተባለች ተጠርጣሪን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ምርመራ ጊዜ መስጠት አስፈላጊ አለመሆኑን ገልጾ÷ በ10 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንድትፈታ ፈቅዷል።
 
በታሪክ አዱኛ
Exit mobile version