Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ህዝበ ሙስሊሙ ረመዳንን በልዩ ፀሎትና መተሳሰብ እንዲያሳልፍ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጅ ኡመር ኢድሪስ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህዝበ ሙስሊሙ ታላቁ የረመዳን ወርን በልዩ ፀሎትና መተሳሰብ እንዲያሳልፍ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጅ ኡመር ኢድሪስ ጥሪ አቀረቡ፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጅ ኡመር ኢድሪስ ጥሪ ውን ያቀረቡት የረመዳን ፆምን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ነው።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጅ ኡመር ኢድሪስ  በመልእክታቸው፥ መስጅዶች መዘጋታቸው የጀመአና የጁምአ ሰላት የማይፈፀምበት መሆኑ የዘንድሮውን ረመዳን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

አያይዘውም ጾሙ ራስን ከመጣው ወረርሽኝ በመጠበቅ የመጣው ፈተና እንዲነሳ ተግተን የምፀልይበት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

“ለዚህ ለተከበረ ወር ያደረሰንን አሏህን በማመስገን መልካም ስራዎችን ለማብዛት ልንጠቀምበትም ይጠበቅብናል” ብለዋል።

ከዚያም ባለፈ ኡለማዎች በወሰኑትና መንግስትም ባስቀመጠው መመሪያ መሰረት መንፈሳዊ ተግባራትን በቤት ብቻ መከወን ጊዜው የጠየቀው ግዴታ መሆኑን ተቀዳሚ ሙፍቲ  አስምረውበታል።

ለወትሮው በዚህ ወር በመስጂዶች በሰፊው የሚካሄደው የዘካ መስጠት የማስፈጠርና  የመረዳዳት ልምድም ለቫይረሱ በማያጋልጥ በቤቶች እንዲቀጥልም አሳሰበዋል።

ከመስጂዶች ውጭ በመኖሪያ አካባቢዎች አንዳንድ ቦታዎች ላይ የሚስተዋለው በጀመአ ለመስገድ የሚደረግ ጥረትም አጋላጭ በመሆኑ መቆም አለበትም ነው ያሉት።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጅ ኡመር ኢድሪስ የረመዳን ፆም  ጨረቃ ከታየች ረቡእ ምሽት ወይም  ሀሙስ ፣ ካልታየች ደግሞ አርብ እለት  እንደሚጀምር ገልጸዋል ።

በሀብታሙ ተክለስላሴ

 

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!

https://t.me/fanatelevision

Exit mobile version