አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ስንዴ ከውጪ ሀገር ከማስገባት ወደ መላክ የተሸጋገርነው ባለን ሐብት ዐቅደን ጠንክረን በመሥራታችን ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
አቶ ሽመልስ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ የብልጽግና ጉዟችን ስኬታማ የሚሆነው ኢኮኖሚያችንን ከውጭ ድጋፍ ማላቀቅ ስንችልና ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት መቀነስ ስንችል ነው ብለዋል፡፡
ይህንንም ዕውን ለማድረግም በዕቅድ ሲሠራ መቆየቱን ነው ያነሱት፡፡
ቀደም ባሉ ጊዜያት መንግስት ስንዴ ከውጭ ለማስገባት በርካታ ቢሊየን ዶላሮችን ሲያወጣ እንደነበር ጠቅሰው÷ ይህም ለሌሎች ልማቶች ማዋል ይገባ የነበረውን ሐብት በማባከን የሀገርን ምጣኔ ሐብት ጎድቷል ነው ያሉት፡፡
መንግስት ለሕዝቡ ቃል ከገባው አንዱ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ምርጥ አምሥት በጥሩ የምጣኔ ሐብት ደረጃ ላይ ከሚገኙ ሀገራት አንዷ እንድትሆን ማስቻል መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ለዚህም በሕዝባችን የሰው ኃይል እና በሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ በሚመረቱ ምርቶች ላይ የተመሰረተ የምጣኔ ሐብት ዕድገት ለማረጋገጥ የተለያዩ ዕቅዶች ተይዘው ሲሰራ መቆየቱን ነው ያስረዱት፡፡
በኢትዮጵያ ÷ ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ መሠራት ያለባቸውን ሥራዎች ለይተን በማቀድ እያከናወንን ነው ያሉት አቶ ሽመልስ ÷ የሀገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ ደግሞ አንዱና ዋነኛው መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በማምረት ሂደት አርሶ አደሩ እየተጫወተ ያለው ሚና አይተኬ ስለመሆኑም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
ክልሉ ወቅት ሳይጠበቅ ዓመቱን በሙሉ ለማረስ የአርሶ አደሩን መሬት በኩታ ገጠም የማደራጀት፣ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር የማከፋፈል እንዲሁም ሙያዊ ክትትል የማድረግ ሥራ እየሠራ መሆኑንም ነው ያረጋገጡት፡፡
በክልሉ ከፍተኛ የስንዴ ምርት እንደሚጠበቅ ጠቁመው÷ ለአብነትም በሰሜን ሸዋ ዞን 16 ወረዳዎች 60 ሺህ ሄክታር መልማቱንና ከወዲሁ ተሥፋ ሰጪ ውጤት መኖሩን አመላክተዋል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!