Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያን የልዩ ቡና ማስተዋወቂያ ኤክስፖ በኦሬገን ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን የልዩ ቡና ማስተዋወቂያ ኤክስፖ በኦሬገን ግዛት ፖርትላንድ ከተማ ተካሄዷል።

የኢትዮጵያን ልዩ ቡና ለማስተዋወቅ የተዘጋጀው መርሐ-ግብር ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከቡናና ሻይ ባለስልጣን እንዲሁም ከኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር በተውጣጡ ኃላፊዎች ተከፍቷል።

በቡና ምርት እና ለዘርፉ አስፈላጊ ቴክኖሎጂዎችን በማምረት ከሚታወቁ ድርጅቶች ጋር ገንቢ ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከኢሊ ካፌ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራርሟል።

ይህም ልምዶችን ለመለዋወጥ እና ለባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ለማድረግ እንደሚያስችል ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ቡና ምርትና ምርታማነት፣ የግብይት ስርዓትን ለማዘመን እየተወሰዱ ያሉ የፖሊሲ ማሻሻያዎች እና እየገጠሙ ባሉ ማነቆዎች ዙሪያ ማብራሪያ መቅረቡን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያን የቡና ልማት እና የምርት ሂደት በሳይንሳዊ መንገድ ደረጃውን ጠብቆ ከማስኬድ አኳያ እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ዙሪያም ገለጻ ተደርጓል።

የቡና ኤክስፖው በሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች የኢትዮጵያ ልዩ ቡና እንዲቀምሱ እና ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም እንዲገነዘቡ ያስቻለ እና በዘርፉ ከተሰማሩ የተለየዩ ሀገራት ድርጅቶች ጋር ትስስር ለመመስረት እድል የፈጠረ መሆኑንም ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።

Exit mobile version