አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ32 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አስታውቋል።
የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) ÷ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተለይ አገልግሎትን ከማስፋትና ተደራሽነትን ከማሳደግ አኳያ በልዩ ትኩረት መሰራቱን አንስተዋል።
በዚህም አጠቃላይ የድርጅቱን የኦፕሬሽን አገልግሎት መጠን 4 ሚሊየን 85 ሺህ 765 ቶን ለማድረስ ታቅዶ 4 ሚሊየን 131 ሺህ 929 ቶን በማድረስ ከእቅዱ በላይ መፈፀሙን ገልጸዋል።
በጭነት ማጓጓዝ አገልግሎት የድርጅቱንና የኪራይ መርከቦችን በመጠቀም 2 ሚሊየን 885 ሺህ በላይ ቶን በማጓጓዝ ከእቅድ በላይ ተከናውኗል ብለዋል።
በዚህ መሰረትም የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ32 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።
በተጠቀሰው ወራት በጭነት አስተላላፊነት አገልግሎት በኩል በመልቲሞዳል የትራንስፖርት ስርዓት 66 ሺህ 194 ኮንቴይነር ለማጓጓዝ ታቅዶ 70 ሺህ 742 ኮንቴይነር በማጓጓዝ የተሳካ ስራ መከናወኑን ጠቁመዋል።
ለሀገር ልማት በተለይም ለግብርና ስራዎች ግብዓትን በማስገባት ረገድ የላቀ አፈፃፀም መታየቱንም ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
በቀጣይም አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ የታገዘና ዓለም አቀፍ ተደራሽነትን ለማስፋት ተቋሙ ግዙፍና ዘመናዊ የዳታ ማዕከል እያስገነባ እንደሆነ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡