አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለመደገፍ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጳውሎስ በርጋ÷ ዘርፉ እንዲያገግም በአጭር፣ መካከለኛና ረጅም ጊዜ የሚሠሩ ሥራዎች ተለይተዋል ብለዋል፡፡
በልዩ ሁኔታ ድጋፍ ለማድረግ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸው÷ በቅርቡም ወደ ትግራይ በማቅናት አጠቃለይ ሥራዎች ይጀመራሉ ማለታቸውን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት መረጃ ያመላክታል፡፡
የትግራይ ክልል ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ መሀሪ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው÷ ኢንተርፕራይዞቹ በተለያየ ደረጃ ውድመት እንደረሰባቸው እና እስካሁን ሥራ የጀመረ አለመኖሩን አረጋግጠዋል፡፡
የደረሰው ውድመት ከፍተኛ በመሆኑ ለክልሉ የሚመጥን መመሪያ ተዘጋጅቶ ዕዳ የሚሠረዝበትና አዳዲስ ብድሮች በፍጥነት ተደራሽ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲመቻች እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
እነዚህን ኢንተርፕራይዞች በፍጥነት ወደ ሥራ ማስገባት በዘርፈ ብዙ ችግር ውስጥ ያለውን የትግራይ ሕዝብ መታደግ በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።