የሀገር ውስጥ ዜና

የብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን የቅድመዝግጀት ስራውን ማጠናቀቁ ተገለፀ

By Mikias Ayele

April 24, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ ተሃድሶ የቅድመ ዝግጅት ሥራውን በማጠናቀቅ ወደ ተግባር ሥራ ለመግባት የሚችልበት ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለፀ፡፡

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም እንዲሁም የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ እና የምክር ቤቱ አባላት በተገኙበት የኮሚሽኑ የሶስት ወር አፈፃፀም ተገምግሟል፡፡

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ብናልፍ አንዷለም ከተቋቋመ 3 ወር የሆነው የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሲሠራ መቆየቱን እና ሥራው ውጤታማ እና የኮሚሽኑን ተልዕኮ ግልጽ ማድረግ የቻለ መሆኑ ገልፀዋል።

ኮሚሽኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራውን በማጠናቀቅ ወደ ተግባር ሥራ ለመግባት የሚችልበት ደረጃ ላይ መድረሱንም አብራርተዋል።

ኮሚሽኑ በ3 ወራት ጊዜ ውስጥም ከክልሎች ጋር ውይይት የማድረግ እና የመስክ ምልከታ ማካሄዱን የጠቆሙት ሰብሳቢው ከክልሎች ጋር በተደረጉ ውይይቶች የኮሚሽኑ ተልዕኮ ላይ ግልፅነት መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ ተዋጊዎችን መረጃ የማጥራት ሥራ በመሥራት ኮሚሽኑ በሰኔ ወር  የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ መደበኛ ሕይወት የመመለስ ሥራውን ለመጀመር መታቀዱ በውይይቱ ተነሥቷል።

በትግራይ ክልል የቡድን መሣሪያ የማስፈታት የመጀመሪያ ሥራ የተጀመረ ሲሆን ቀጣይ የማስፈታት ሥራ እና ታጣቂዎችን የመመዝገብ ሥራ መሥራት እንደሚገባ መገለፁን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡