የሀገር ውስጥ ዜና

ከትግራይ ሕዝብ የሰላም እና የፍቅር መልዕክት ይዤ መጥቻለሁ – አቶ ጌታቸው ረዳ

By ዮሐንስ ደርበው

April 23, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከትግራይ ሕዝብ የሰላም እና የፍቅር መልዕክት ይዤ መጥቻለሁ፤ የትግራይ ሕዝብም ጦርነት ሰልችቶታል ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መስተዳድር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ ተናገሩ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ወዳጅነት አደባባይ ‘ጦርነት ይብቃ፤ ሰላም እናጽና’ በሚል መሪ ሐሳብ የምስጋና እና የዕውቅና ሥነ ስርዓት ተካሒዷል፡፡

በሥነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ጌታቸው ረዳ÷ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ በስምምነቱ መሠረት ሕዝቡን እና ክልሉን የሚጠቅሙ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

ለስምምነቱ በፍጥነት መተግበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ላሳዩት ከፍተኛ ድፍረት የተሞላበት ቁርጠኝነት በትግራይ ሕዝብ ስም እናመሰግናለን ብለዋል፡፡

ቀሪ ሥራዎችም በተያዘው ፍጥነት ልክ እንዲከናወኑ ጠይቀዋል፡፡

በትናንትናው ዕለትም የሕዝብ ትራንስፖርት በአፋር በኩል መጀመሩን ጠቁመው ይኸው አገልግሎት በአማራ ክልል በኩል እንዲጀመርም በጋራ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ መፍታት እተቻለ በክፉ የጠብ መንጃ ማንሳት አባዜ ላለፉት ሁለት ዓመታት እጅግ ደም አፋሳሽ ጦርነት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ ብዙ መሻሻሎች እንዳሉ ገልጸው÷ በቀጣይም የተቀሩት የስምምነቱ አካላት በሚገባ ተፈፃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የትግራይ ሕዝብ ጦርነት እንደሰለቸውና ከዚህ በኋላ ጠብመንጃ የማንሳት ፍላጎት እንደሌለው አንስተዋል፡፡

እስካሁን ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖች የሚመለሱበት እና በክልሉ የተቋረጠው የመማር ማስተማር ሥራ በተቻለ ፍጥነት ወደነበሩበት እንዲመለስ ጠይቀዋል፡፡ በወንድም የአማራና የአፋር ሕዝብ መካከል ሳይገባ የተፈጠረው ግጭት ታሪክ የማይሽረው ጠባሳ አሳድሮ አልፏል ያሉት አቶ ጌታቸው÷ አሁን ግን ሰላም በሚጸናበት ጎዳና መራመድ ይገባል ብለዋል፡፡

ግጭትና ጦርነትን ወደ ጎን ትቶ የሁሉም አካባቢ በተለይም የትግራይ አርሶ አደር የናፈቀውን ግብርና ማከናወን እንደሚፈልግም ነው የተናገሩት፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!