የሀገር ውስጥ ዜና

የክርስትና ሃይማኖት አባቶች ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

By Meseret Demissu

April 18, 2020

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10፣2012( ኤፍ.ቢ.ሲ) የክርስትና ሀይማኖት አባቶች ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማትያስ ÷በመላ አገሪቱ ለገጠርና ለከተማ፣ ከአገር ውጪ፣ የአገሪቷን ዳር ድንበር እየጠበቁ ለሚገኙና በሕመም ላይ ላሉ እንዲሁም ለሕግ ታራሚዎች እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

የበዓሉም መሰረት ”ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛና ስለ ደህንነታችን ሲል በለበሰው ስጋ ታመመ፣ ሞተ፣ ተቀበረ፣ በሶስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ፣ ሞትና መቃብርን አጥፍቶ ተነሳ የሚለው ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ክርስቶስ ይህንን ሁሉ መከራ የተቀበለውም ሰዎች የተከተሉትን የተሳሳተ ምርጫ ለማረምና ቤዛ ለመሆን መሆኑን የገለጹት ብጹዕነታቸው ”በሕመሙ ሕመማችንን፣ በሞቱ ሞታችንን፣ በመቃብሩ ሞትና መቃብርን አስወግዶ፣ በትንሳኤው ትንሳኤያችንን ሰጥቶናል” ብለዋል።

ብጹዕነታቸው አያይዘውም እግዚአብሔር ፍጡራኑን አያጠፋም “አሁን የመጣውን ኮሮና የተባለውን በሽታ ለመከላል እግዚአብሔር እውቀቱን ከሰጣቸው ባለሙያዎች የሚተላለፈውን መልዕክት መተግበር እንጂ እሱ ያውቅልናል የሚለው ቸልተኝነት ማሳየት እግዚአብሔርን መፈታተንና ኃጥያትም ነው” ብለዋል።

የቅድስት ቤተክርስቲያን ምድራዊ ወኪል በሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ አማካኝነት ምዕመናን ቤት ሆነው እንዲጸልዩ የተላለፈው ውሳኔ እንዲሁ ዝም ብሎ አለመሆኑም ሊታወቅ ይገባል ነው ያሉት።

ሲኖዶስ ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው እግዚአብሔር አንድም ሰው እንኳን በጥንቃቄ ጉድለት እንዲጎዳ ስለማይፈልግ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በስውር መጾምና መጸለይ ስለሚፈቀድም ጭምር ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ምዕመኑም ካህናቱም እስካሉ ድረስ እግዚአብሔር ምህረቱን በላከ ጊዜ በቤተክርስቲያን ውስጥ በአንድ ላይ ሆኖ መጸለይ፣ ማመስገንና ማስቀደስ፤ ማምለክና መቁረብ እንደሚቻል መገንዘብ ተገቢ ነው ብለዋል ብጹዕነታቸው።

”በመሆኑም አሁንም ቢሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ባስተላለፈውና ወደፊትም እንደ አስፈላጊነቱ በሚያስተላልፈው ሲኖዶሳዊ ብይን መሰረት በየቤታችሁ ሆናችሁ ከልብ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ በሽታውን እንድትከላከሉ፤ ለተቸገሩ ወገኖችም ያቅማችሁን አድርጉ” ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም ”የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ከማክበር የበለጠ ቀን የለም” ብላለች።

የቤተክርስቲያኗ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ”የዘንድሮው በዓላችን በሃዘንና በጨለማ የተከበበ ቢመስለንም በተስፋ የተሞላን ሆነን እናከብረዋለን” ብለዋል።

”ምክንያቱም ጌታችን የሥጋውን ድካም ሞትን ድል በማድረግ በመንፈሳዊነት እንዳሸነፈ እኛም የሥጋን ድካም በመንፈሳዊነት እንደምናሸንፍ አውቀን በዚህ ወቅት የዓለም ደዌ ሆኖ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ እርሱ በትንሣኤው እንዲሽርልንና እንዲያጠፋልን የጀመርነውን የጸሎትና የንስሐ ልመና አምላካችን ሆይ እንደቸርነትህ ብዛት ማረን፣ ይቅር በለን በማለት አጠናክረን ልንቀጥል ያስፈልጋል” ነው ያሉት።

”ይህን ክፉ ቀን ማለፍ የምንችለው በእምነትና በፀሎት ነውና እንበርታ፤ እንቆቅልሽ የሆነብን ነገር ተፈቶ አዕምሮአችን ሰላምና ደስታ እንዲያገኝ በተለያየ መንገድ ይህን በሽታ ለመከላከል ለሚሰሩና ለሚተጉ እንዲሁም በጎ ለሚያደርጉ ሁሉ እግዚአብሔር ጥበቃውንና ፀጋውን እንዲያበዛላቸው ምኞታችንና ጸሎታችን ነው” በማለት ለምዕመኑ ጥሪ አቅርበዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ክርስቲያኖችም በዚህ የትንሳኤ ክብረ በዓል ጥንቃቄ በተሞላው መንገድ ለወንድሞቻውና ለእህቶቻው፣ ለአገራቸው አስፈላጊውን እገዛ እና እርዳታ እንዲያደርጉም መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ እየሱስ ፕሬዚዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ  በበኩላቸው ÷እንኳን ለ2012 ዓ.ም ለጌታችንና ለመድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓል አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

”የኮሮና ቫይረስ ክስተት አድማሱን እያሰፋና ጥቃት እያደረሰ በመሆኑባሁኑ ወቅት  ሁሉም ዜጋ ራሱን በመጠበቅ ለወገኑ መጠንቀቅና ከመንግስት፣ ከባከሙያዎችና ከሀይማኖት መሪዎች የሚሰጠውን ምክር ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል ”ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ጻድቁ  አብዶ  ለመላው ህዝበ ክርስቲያን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ፓስተር ጻድቁ በመልዕክታቸው ”ትንሳኤው ብርሃን ጨለማን ያሸነፈበት፣ ሞት ድል የተነሳበት፣ሀሰት ተንኮል ጥላቻ በፍቅርና በዕውነት የተረቱበት ÷ብርሃን ህይወትና ፍቅር ርህራሄ አሸንፈው እና ድል ነስተው ዘመነ ፍዳ በዘመነ ምህረት የተለወጠበት ትንሳዔ ነው”ብለዋል፡፡

አክለውም  ”ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ዓለም  በኮቪድ 19 ምክንያት“በፍርሃትና በጭንቀት ውስጥ  የወደቀበት ነው÷  ቫይረሱን ለመዋጋት ግንባር ቀደም ሆነው እየሰሩ ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች፣በልዩ ልዩ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ማለሙያዎችንና በጎ አድራጊዎችን ልናመሰግን እንወዳለን ”ብለዋል፡፡

 

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!

https://t.me/fanatelevision