የሀገር ውስጥ ዜና

መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል ደንጎላት የተለያዩ የቡድን መሳሪያዎችን ተረከበ

By ዮሐንስ ደርበው

April 19, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዛሬው ዕለት የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል ደንጎላት የተሰበሰቡ የመጀመሪያ ዙር የተለያዩ የቡድን መሳሪያዎችን ተረከበ፡፡

መንግሥት እና ህወሓት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈራረሙትን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ የማድረግ አካል የሆነው የህወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

በስምምነቱ መሰረትም የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በመጀመሪያው ዙር ትጥቅ የማስፈታት ሂደት ከባድ መሣሪያዎችን በሁለተኛው ዙር ደግሞ የአየር ኃይል መሳሪያዎችን ከህወሓት መረከቡ ይታወቃል።

ባለፈው ሳምንትም ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ጋር በትጥቅ ማስፈታት ሂደቱ ላይ ውይይት ያደረጉት የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጀኔራል ደርቤ መኩሪያ÷ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 16 የቡድን መሳሪያዎች ርክክብ እንደሚደረግ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በቀጣይ ቀናትም በተለያዩ ካምፖች የሚገኙ የቡድን መሳሪያዎች ርክክብ እንደሚፈጸም ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በስፍራው የተገኙት የመከላከያ ሠራዊት ተወካይ ኮሎኔል ጉደታ ኦፍካ÷በዛሬው ዕለት ሞርታር፣ ዲሽቃ እና መሰል በርካታ የቡድን መሳሪያዎችን መረከባቸውን ገልጸዋል።

የህወሓት ተወካይ ሙሉጌታ ገብረ ክርስቶስ በበኩላቸው÷ በስምምነቱ መሰረት የህወሓት ታጣቂዎች የቡድን መሳሪያዎችን በመፍታት ለኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት እያስረከቡ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ተወካዮቹ አክለውም የትጥቅ ማስፈታት ሂደቱ በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

መንግስት እና ህወሓትም ለሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚነት አዎንታዊ እርምጃዎችን እየወሰዱ ስለመሆናቸው ነው ያመላከቱት፡፡

የሰላም ስምምነቱ አተገባበርም ለሀገር ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ተሥፋ የሚጣልበት ሆኗል ነው ያሉት።