አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ ማኅበረሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡
ስርጭቱን ለመግታትም ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ እና ለተግባራዊነቱም የሁሉም ቅንጅት ወሳኝ ነው መባሉን የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
በሽታው ባልተከሰተባቸው አካባቢዎችም ጭምር ቅድመ ጥንቃቄን መርኅ በማድረግ የግል እና የአካባቢን ንፅሕና ለመጠበቅ በቅንጅት መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ነው የተመለከተው፡፡
እንዲሁም ሕብረተሰቡ የኮሌራ የበሽታ ምልክት የሚታይባቸውን ሰዎች በፍጥነት ወደ ተቋቋመው ጊዜያዊ የሕክምና መስጫ ማዕከል በማድረስ የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዲወጣ ኢንስቲትዩቱ ጠይቋል፡፡