አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች በመልዕክታቸው ÷ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ ያለውን ፍቅር ሊገልፅ የህይወት ዋጋን ከፍሎ ፤ ሞትን ደግሞ ድል ነስቷል ብለዋል፡፡
በዚህ ተግባሩ ለሰው ልጆች ሁሉ ፍቅርን፣ መዋደድን፣ መከባበርንና መተሳሰብን እንዲሁም አንዳችን ለሌላችን መኖርን አስተምሯል ነው ያሉት፡፡
እኛም የትንሳኤ በዓልን ስናከብር ፈጣሪ የሰጠን ሀገር ለሁላችንም በቂ ስለሆነች ጥላቻን እና መነቋቆርን ትተን ከራሳችን እና ካስቀየምነው ሁሉ ጋር በመታረቅ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች በዓሉን ሲያከብሩ ከሀገር ባለውለታዎች ፣ከአቅመ ደካሞች እንዲሁም ጠያቂ ከሌላቸው ወገኖች ጋር በፍቅር ማዕድ እየተጋሩ በአብሮነት እንዲያከብሩም ጥሪ አአቅርበዋል፡፡
የትንሳኤ በዓል የፍቅር፣ የመከባበር፣ የመተሳሰብና የአብሮነት እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡