ቢዝነስ

በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በትልቅነቱ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት የሶስተኛ ደረጃን ይይዛል – አይ ኤም ኤፍ

By Mekoya Hailemariam

April 14, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)  በያዝነው የፈረንጆቹ 2023 ዓመተ ምህረት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በትልቅነቱ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት የሶስተኛ ደረጃን እንደሚይዝ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) አመለከተ።

አይ ኤም ኤፍ የ2023 የዓለም ኢኮኖሚ አፈፃፀም ትንበያውን ይፋ አድርጓል።

ተቋሙ ኢትዮጵያን በተመለከተ አውጥቶት የነበረውን ትንበያ ከልሶታል።

ይህንን ትንበያ ዋቢ አድርጎ ቢዝነስ ዴይሊ አፍሪካ እንደዘገበውም፥ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት መጠን 156 ነጥብ 1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር  ይደርሳል።

ይህም ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የትልቅ ኢኮኖሚ ባለቤትነት ስፍራን ከኬንያ እንድትረከብ የሚያደርጋት መሆኑን ነው ያመለከተው።

ትንበያው፥ ምስራቅ አፍሪካ ላይ  እስክ አውሮፓውያኑ 2028 ድረስ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገቱን በመቀጠል የቀጣናው ቀዳሚ ግዙፍ ኢኮኖሚነቱን ይዞ እንደሚቆይ ጠቅሷል።

ናይጄሪያ በ506 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር እና ደቡብ አፍሪካ በ399 ቢሊየን ዶላር የአገር ውስጥ ምርት እድገት መጠን 1ኛ እና 2ኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ ሆነው እንደሚቀጥሉ አስቀምጧል።

ትንበያው ኢትዮጵያ በግብርና እና ማምረቻ ኢንዱስትሪ ልማት ቀጥተኛ የውጭ እንቨስትመንትን የመሳብ አቅሟን ከፍ እንደሚያደርግ ነው የተመለከተው።

ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በዋጋ ግሽበት፣ በጦርነት እና ድርቅ ምክንያት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ቀንሶ እንደነበር የጠቆመው የአይ ኤም ኤፍ ሪፖርት፥ ዘንድሮ 6 በመቶ እንደሚያድግ ተንብይዋል።

ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ  ጋር በመሆን በተሻለ ሁኔታ የውጭ ባለሀብቶችን እንደምትስብም ነው የጠቆመው።