Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በትዳር ውስጥ የሚከሰቱ ፈተናዎችን እንዴት ማሸነፍ ይቻላል?

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የትዳር ፍቺ ስነ-ልቦናን እንደሚጎዳ፣ ለጸጸት እንደሚዳርግ እንዲሁም የልጆችን የወደፊት እጣ ፈንታ ከማጨለም ባሻገር በሀገር ላይ ኪሳራ እንደሚያደርስ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

የትዳር አማካሪና የማህበረሰብ ሳይንስ ባለሙያ የሆኑት ደረጀ ግርማ ÷ትዳር የትዳር ጓደኛ በህይወት እስካለ (እስካለች) ድረስ መፍረስ የማይጠበቅበት፣ እንዲፈርስ የማይበረታታ ዘለቄታዊ ተቋም መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ሰዎች በሐይማኖት ተቋማት ወደ ጋብቻ ውስጥ ሲገቡ በማግኘትና በማጣት፣ በሀዘንና በደስታ፣ በሙላትና በጉድለት በአንተ(አንቺ) ብቻ ፀንቼ̎ ብለው ቃል ኪዳን እንደሚያስሩ ገልጸዋል፡፡

ጋብቻ ሶስት ደረጃዎች እንዳሉት የሚገልጹት አቶ ደረጀ÷ከ0 እስከ 5 ዓመት ያለው የመጀመሪያ ደረጃ  መሆኑን ያብራራሉ፡፡

በዚህ ደረጃ ላይ የተለያዩ ፈተናዎች እንደሚያጋጥሙና ግጭቶችም ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቅሰው÷የሁለተኛው ደረጃ ላይ ደግሞ የመስከንና የመተሳሰብ ጊዜ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሶስተኛው ደረጃ የሃላፊነት ጊዜ ሲሆን÷በዚህ ምዕራፍ ልጆች እንደሚኖሩ፣ ሃላፊነት እንደሚበዛ እንዲሁም ግጭቶች እየቀነሱ የሚሄዱነትና የተስፋም ጊዜ መሆኑም ገልጸዋል፡፡

የትዳር ፍቺ በከፍተኛ ደረጃ የሁለቱንም ፆታ ስነ-ልቦና ይጎዳል የሚሉት የማህበረሰብ ሳይንስ ባለሙያው÷ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለንተቀባይነት እንደሚያሳጣም ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም ፍቺ መንፈሳዊ ነገርንና ኢኮኖሚን እንደሚጎዳ፣ የትኛውም የሃይማኖት አስተምህሮ ፍችን እንደማይደግፍ እና ፍቺ ለጸጸትም እንደሚዳርግ አክለዋል፡፡

ፍቺ የልጆች የወደፊት እጣ ፈንታ ከማጨለም ባሻገር በሀገር ላይ ትልቅ ኪሳራ እንደሚያደርስ ና ዘመድም ሆነ ሌላ ሰው በትዳር ውስጥ ጣልቃ መግባት ከጀመረ ትዳሩ አደጋ ውስጥ እንደሚወድቅ  ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡

ባለትዳሮች ከተግባቡ፣ ከተመካከሩና ከተከባበሩ ሦስተኛ ወገን ትዳር ለማፍረስ ቦታ እንደማይኖረውም ባለሙያው  ተናግረዋል፡፡

ትዳርን ከፍቺ አረንቋ ለማውጣት ጥንዶች የሚከፍሉት መስዋዕትነት እንደሚኖር፣ ይህ መስዋዕትነትም ለልጆች ሲባል ሊከፈል የሚችል እንደሆነ ይገለጻል፡፡

ጥንዶች ወደ ትዳር ከመግባታቸው በፊት ሊያስተውሉም እንደሚገባ  ጠቁመው÷በእቅድ እና በትኩረት የተገነባ ትዳር ከሁሉም የበለጠ ጠንካራ መሰረት እንደሚኖረው አስርድተዋል፡፡

የማህበረሰብ ሳይንስ ባለሙያ ÷ጋብቻ ማሕበራዊ ተቋም እንደመሆኑ መጠን ተጋቢዎች በሰከነ አዕምሮ ሊጠብቁት ካልቻሉ ሌላ አካል ማንም ሊጠብቀው እንደማይችል አስገንዝበዋል፡፡

በየሻምበል ምህረት

 

Exit mobile version