አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በእንግሊዝ የንጉሳውያን ቤተሰብ የመቃብር ሥፍራ ያረፈው የልዑል ዓለማየሁ አፅም ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ተጠየቀ፡፡
ጥያቄው አሁን ላይ እንደ አዲስ የቀረበው ለእንግሊዙ የንጉሳውያን ቤተሰብ የአሁኑ ንጉስ ቻርለስ ሲሆን በልዑሉ የሕይወት ታሪክ ላይ የተፃፈ አዲስ መፅሐፍ ለጥያቄው እንደ አዲስ መነሳት ምክያት መሆኑን ሜይል ኦንላይን የተሰኘው የሀገሪቷ የዜና ምንጭ ዘግቧል፡፡
ልዑል ዓለማየሁ በ19ኛው ክፍለ-ዘመን አጋማሽ በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉስ የነበረው የዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ልጅ እንደነበረ ይታወቃል፡፡
በፈረንጆቹ 1978 ላይ በቀላሉ ሊድን በሚችል የኒሞኒያ ሕመም ተይዘው በ18 ዓመታቸው ያረፉት ልዑል ዓለማየሁ አስከሬናቸው እንግሊዝ በሚገኘው ዊንድሶር የንጉሳውያን ቤተሰብ የመቃብር ሥፍራ ማረፉም በመረጃው ተመላክቷል፡፡
እንግሊዝ ኢትዮጵያን በፈረንጆቹ 1868 ላይ ስትወር ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ከወታደሮቻቸው ጋር አብረው ተፋልመው በመጨረሻዋ ሠዓት በእንግሊዝ እጅ ከመውደቃቸው በፊት ራሳቸውን ማጥፋታቸውን ታሪክ ዘግቦታል፡፡
ንጉሱ እራሳቸውን ካጠፉ በኋላም ልጃቸው ልዑል ዓለማየሁ ከአባታቸው ቤተ-መንግስት ተይዘው ወደ እንግሊዝ እንደተወሰዱ ይነገራል፡፡
ልዑል ዓለማየሁ በንግስት ቪክቶሪያ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ እንደነበሩመ ይወሳል፡፡
ልዑሉ በእንግሊዝ ወታደራዊ ትምህርት መማራቸውም ተመላክቷል፡፡
እንደሚታወሰው በታሪክ ተመራማሪው አሉላ ፓንክረስት የሚመራው የኢትዮጵያ ቅርሶች አስመላሽ ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ ሲሰራ ቆይቷል፡፡