አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ751 ሚሊየን በላይ ችግኝ የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ባለሙያ አቶ መስፍን ባልቻ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በክልሉ ሁሉም ዞኖች ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሚውል ችግኝ ለማዘጋጀት የጋራ እቅድ ወጥቶ እየተሰራ ነው፡፡
በዚህ መሰረት ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በክልል ደረጃ 751 ሚሊየን 666 ሺህ ችግኝ እየተዘጋጀ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
የዝግጅት ስራው 1 ሺህ 830 በሚሆኑ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች እየተከናነ መሆኑን ጠቁመው ÷ እስካሁንም ከ352 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ችግኝ ለቆጠራ መድረሱን ጠቅሰዋል፡፡
የሚዘጋጁት የችግኝ አይነቶችም ለደን ልማት የሚውሉ፣ የፍራፍሬ ዝርያዎች፣ የቀርከሃ ችግኝና ሌሎች የችግኝ አይነቶች መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
ከችግኝ ዝግጅቱ ጎን ለጎን የመትከያ ቦታ እየተለየ ነው ያሉት አቶ መስፍን ÷ እስካሁንም 37 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መለየቱን አንስተዋል፡፡
ለመትከያ አገልግሎት ለሚውሉ ቦታዎች በቴክኖሎጂ በመታገዝ ካርታ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን የማዘጋጀት ስራ እተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ