አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ተጨማሪ 7 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ይህን ተከትሎም በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 92 ደርሷል።
ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰባቱም ግለሰቦች ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፥ ከእነዚህም ውስጥ 6ቱ የጉዞ ታሪክ ያላቸው እና በለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ፥ አንዷ ደግሞ የጉዞ ታሪክ የሌላትና ንክኪ እንዳላት በመጣራት ላይ እንደሚገኝ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።
በዚህም መሰረት የ21 ዓመት እና የ51 ዓመት እድሜ ያላቻው ኢትዮጵያውን ከአሜሪካ የመጡ፤ እንዲሁም የ76 ዓመት እና የ34 ዓመት እድሜ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከስዊድን የመጡ ሲሆን፥ ሁሉም በለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
በተጨማሪም የ32 ዓመት ኢትዮጵያዊ የጀርመንና የቤልጂየም የጉዞ ታሪክ ያለው እንዲሁም የ39 ዓመት ኢትዮጵያዊ ደግሞ ከጃፓን የመጣ ሲሆን፥ ሁለቱም በለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
የ14 ዓመት ሴት ኢትዮጵያዊት ደግሞ የጉዞ ታሪክ እንደሌላት የተገለፀ ሲሆን፥ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ እንደነበራት በመጣራት ላይ የሚገኝ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል።
አሁን ላይ 72 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸው በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሲሆኑ፥ አንድ ሰው ደግሞ በጽኑ ህክምና ላይ
የሚገኝ መሆኑን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።
ሚኒስትሯ መጭውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ የሚካሄዱ የበዓል ግብይቶችም አካላዊ ርቀትን በጠበቀ መልኩ በጥንቃቄ እንዲከወኑም አሳስበዋል።