Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከተጀመረው አዲስ ተላምዶ ጋር የሚጣጣም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራ እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) እንደሀገር ከተጀመረው የለውጥ ጉዞ፣ አዲስ ተላምዶና አቅጣጫ ጋር የሚጣጣም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራ እንደሚያስፈልግ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

ውጤታማ ተግባቦት ለኢትዮጵያ ልዕልና በሚል ርዕስ ለፌዴራል ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች፣ ለክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች የኮሙኒኬሽን ኃላፊዎች እንዲሁም ለመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች ስልጠና እየተሰጠ ነው።

ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በስልጠናው ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የኮሙኒኬሽን ሥራዎች በሕዝቦች መካከል መልካም መስተጋብር በመፍጠርና ችግሮችን በመፍታት ረገድ ጉልህ ሚና እንዳላቸው አመላክተዋል፡፡

የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ መልካም መስተጋብር ለመፍጠር፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን ለማሳካት ጉልህ ሚና የሚጫወት የተግባቦት ዘዴ በመሆኑ በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

በአጀንዳ ቀረጻ ላይ የሚታዩ መሰረታዊ ችግሮችን መፍታት እና ለምን አይነት ጉዳይ ምን አይነት የኮሙኒኬሽን አካሄድ ልንከተል ይገባናል ብሎ ማሰብ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡

ከ200 በላይ የኮሙኒኬሽን አመራርና ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ስልጣና ለ4 ቀናት እንደሚቆይ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የመደመር ትርክት እና የኢትዮጵያ ብልፅግና ጉዞ፣ የሕዝብ ግንኙነት መሰረቶች እና አጀንዳ ቀረጻ፣ የቀውስ ጊዜ ኮሙኒኬሽን፣ የሚዲያ አስተዳደርና ለሕዝብ የሚደረጉ ንግግሮች በሚሉ ርዕሶች ላይ ስልጠናና ውይይት እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡

Exit mobile version