Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኢንዱስትሪዎች የሃይል አቅርቦት ችግርን ለመፍታት አዳዲስ አሰራሮች እየተተገበሩ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢንዱስትሪዎች ላይ የሚስተዋለውን የሃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት አዳዲስ አሰራሮች እየተገበረ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡

በአገልግሎቱ የሃይል አቅርቦት ማስተባበሪያ ሃላፊ አቶ ነብዩ በየነ÷ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ መነቃቃት ከመፈጠሩ ጋር ተያይዞ የኢነርጂ ፍላጎት በፍጥነት እየጨመረ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

ለተፈጠረው የሃይል ፍላጎት ተገቢ ምላሽ ለመስጠትም የአገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል ከጊዜ ወደ ጊዜ  ዘመናዊ እና ቀልጣፋ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

 

በዚህ መሰረት ከፍተኛ ሃይል የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ላይ የሃይል መቆራረጥ ችግርን ለመቅረፍ አዲስ መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ እየተተገበረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

በተለይም የሃይል መቆራረጥ እና ሌሎች መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት የሚያስችል በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ተግባራዊ መደረጉን ነው አቶ ነብዩ  የገለጹት፡፡

 

በዋናው መስሪያ ቤት የኢንዱስትሪ ደንበኞች ሃይል አቅርቦት ማስተባበሪያ ቢሮ በማቋቋም ለሁሉም ክልሎች በአንድ መስኮት አገልግሎት አስፈላጊው ድጋፍ እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 

የኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝ ለማድረግ በአዳማ፣ ድሬዳዋ፣ መቀሌ፣ ባህር ዳር፣ ደሴ፣ ጅማ፣ ሐዋሳና አዲስ አበባ ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች በ226 ሚሊየን ዶላር የተከናወኑ የዲስትሪቢዩሽንና የአቅም ማሳደግ ፕሮጀክቶች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል በወላይታ ሶዶ፣ ሐረር፣ ሻሸመኔ፣ ደብረማርቆስ፣ ጎንደርና ኮምቦልቻ በሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የዲስትሪቢውሽን መስመር መልሶ ግንባታ እና አቅም የማሳደግ ፕሮጀክት ስራ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አሁን ላይም የአዲስ አበባ ትራንስሚሽንና ዲስትሪቢዩሽን የመልሶ ግንባታ እና የአቅም ማሳደግ ፕሮጀክት እንዲሁም ዲስትሪቢዩሽን ኔትዎርክ ማሻሻያ ፕሮጀክት እየተከናወነ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በተመሳሳይ በቢሾፍቱ፣ ደብረብርሃን፣ ሱሉልታ፣ አምቦ፣ ነቀምት፣ አሶሳ፣ ሆሳዕና፣ ዲላ፣ አሰላና ጅግጅጋ ከተሞች የዲስትሪቢዩሽን ኔትዎርክ ማሻሻያ ፕሮጀክት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በቅርቡም 23 የማይክሮ ኢኮኖሚ ክትትል የሚደረግላቸው የውጭ ቀጥተኛ ኢንዱስትሪዎች፣ 106 ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ ኢንዱስትሪዎችና ለ29 የአበባ ልማቶች የሃይል አቅርቦት እንዲያገኙ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

በተያዘው ዓመት ለቦሌ ለሚ፣ ቂሊንጦ፣ አረርቲ፣ ሃዋሳ እና አዳማ ኢንዱስስትሪ ፓርኮች እና ሌሎች ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች 640 ሜጋ ዋት ሃይል ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በቀጣይ 4 እና 5 ዓመታት ውስጥ ሊመጡ የሚችሉ የአንዱስትሪ ልማቶችን መሸከም የሚያስችል መሠረተ ልማት እየተገነባ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

 

 

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version