ቴክ

የከፍተኛ ትምህርትን በቴክኖሎጂ በመታገዘ ማስቀጠል በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ውይይት ተካሄደ

By Meseret Awoke

April 16, 2020

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቴክኖሎጂ በመታገዘ የከፍተኛ ትምህርትን ለማስቀጠል በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ውይይት ተካሄደ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ከሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ፕሬዚዳንቶች ጋር የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተማሪዎች ባሉበት ሆነው ትምህርት ማስቀጠል በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ በቪዲዮ ኮንፈረንስ መክረዋል።

በውይይታቸው መማር ማስተማሩ ከገፅ ለገፅ ውጪ ባለው ሁኔታ በቅድመ ምረቃ፣ ድህረ ምረቃ እና ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ዘንድ እንዴት ይቀጥል በሚለው ላይ ነው የተወያዩት።

በዚህም የድህረ ምረቃና ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ካሉበት ሆነው በኦንላይን እንዲከታተሉ ዩኒቨርስቲዎቹ እንዲያመቻቹና መምህራንም በኦንላይን የሚሰጡ ትምህርቶችን በማመቻቸትና በተለያዩ መንገዶች ተደራሽ በማድረግ እንዲያስቀጥሉ ተብሏል።

ተማሪዎች ካሉበት ሆነው ከንባብ ሳይርቁ ወደፊት በሚገለፁ ዌብሳይቶች በመግባት የተለያዩ የትምህርት ሞጁሎች፣ ፓወርፖይንቶችን፣ ማጣቀሻ መፃህፍት አግኝተው እንዲያነቡ የሚያስችሉ ዝግጅቶች በቅርቡ ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው መመሪያ ተሰጥቷል።

ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመነጋገር ለተማሪዎችና ለመምህራን ለተመረጡ የትምህርትና ምርምር ዌብሳይቶችና መተግበሪያወች ኢንተርኔትን ከክፍያ ነጻ እንዲሆኑ እንዲደረግ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

በየትምህርት ፕሮግራም የተዘጋጁ የኮርስ መሳሪያወችንና አጋዥ የትምህርት መጽሃፍቶች በመለየት ዝግጁ መደረጉ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በዚህም ከ80 ሺህ በላይ መፃህፍት፣ የአንደኛ ዓመት ትምህርት የኮርስ ሞጁሎችና የተለያዩ የመመረቂያ ጥናቶች ዝግጁ መደረጋቸውንና እነዚህም ተደራሽ የሚሆኑባቸው ቴክኖሎጂዎች መመቻቸቱ ተገልጿል።

በውይይቱ ትምህርቶችን በኦንላይን ማስቀጠል ሲባል ምንም እንኳን የአቅርቦትና ፍትሃዊነት ጉዳይ ጥያቄ ሊሆን ቢችልም፤ የተወሰኑትን እንኳን ተደራሽ ለማድረግ መስራት አስፈላጊ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ለሁሉም የትምህርት ፕሮግራሞች ይዘቶችን ተደራሽ የሚያደርግ የዲጂታል ቤተመፃፍህት http://ndl.ethernet.edu.et/ መሆኑንና እንዲሁም http://library.techin.et/ ላይ እንደሚገኙ ተመላክቷል።