አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው ሸኔ ላይ እየተወሰዱ ያሉ ወታደራዊ እርምጃዎች አሁንም መቀጠላቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት መግለጫ÷ የመከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢዎች ከገባ ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ውጤት እየተገኘ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዚህም የሽብር ቡድኑ ይዟቸው የነበሩ በርካታ ቦታዎች መለቀቃቸውን ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ የገለጹት፡፡
ነጻ የወጡት አካባቢዎችም ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው እንዲመለሱ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
ከሽብር ቡድኑ ነጻ በወጡ የተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎች እና ሌሎች መንግስታዊ አገልግሎት የሚሰጡባቸው ተቋማትን መልሶ የማደራጀቱ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ከምዕራብ ወለጋ እና ሆሮ ጉድሩ በስተቀር በሌሎች አካባቢዎች በተለይም በሸኔ ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ዳግም እንዲጀመሩ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
መንግስት ለሽብር ቡድኑ በይፋ ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ በርካታ የቡድኑ አባላት ትጥቃቸውን እያወረዱ ወደ ተሃድሶ ማዕከላት እየገቡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የሰላም ጥረቱንም ለማስተባበር በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመው ኮሚቴ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ አረጋግጠዋል፡፡
የሰላም ሂደቱ በሀገር ሽማግሌዎች እና በአባ ገዳዎች እንዲከናወን ከሕብረተሰቡ የቀረቡትን ጥያቄዎች መንግስት ሙሉ በሙሉ ያከብራል ብለዋል በመግለጫቸው፡፡
የሕዝቡን ፍላጎት ባከበረ መልኩ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚቀጥልም ነው ያመላከቱት፡፡
የሰላሙ ጥሪ አሁንም በመንግስት በኩል እንደተጠበቀ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!