አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በብልፅግና ፓርቲ ምክትል ኘሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ የተመራ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋን ያካተተው የኢትዮጵያ ከፍተኛ የሥራ ልዑካን ቡድን በሶማሊያ የስራ ጉብኝት ዛሬ አደረገ።
ልዑካን ቡድኑ ሞቃድሾ ሲደርስ በሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና አለምአቀፍ ትብብር ሚኒስትር አብሽር ኦማር ጃማ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።
ልዑካን ቡድኑ በሶማሊያ ቆይታው ከሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ እና አለምአቀፍ ትብብር ሚኒስትር እና ከሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል።
በውይይታቸው ረጅም አመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጠንካራ ግንኙት ይበልጥ በሚጎለብትባቸው ሁኔታዎች ላይ የተነጋገሩ ሲሆን፥ በተለይ ደግሞ በፀጥታ እና ንግድ የሃገራቱ ትብብር ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዳይሬክቶሬት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።