አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር በልማት፣ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰራ በኢትዮጵያ የኅብረቱ አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ተናገሩ።
አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ እንዳሉት÷ አውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር በዘርፈ ብዙ የትብብር አድማሶች ላይ ጠንካራ አጋርነት አለው።
በተጨማሪም የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቁመው ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ግንኙነቱ በአንድ ዘርፍ ብቻ ላይ የተንጠለጠለ አለመሆኑን ገልጸው አጋርነቱ በኢኮኖሚና በፖለቲካው መስክ እያደገ መምጣቱን ም ጠቁመዋል፡፡
በተለይም ሰው ተኮር በሆኑ በማኅበራዊ ዘርፎች ላይ አውሮፓ ኅብረትና አባል አገራት ትኩረት ሰጥተው ትብብሩን ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑን ነው የገለጹት።
ይህንንም ተከትሎ በቅርቡ ለማኅበራዊ ልማት የሚውል ከ9 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ የድጋፍ ሥምምነት ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አምባሳደሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ግብርናውን ለማዘመንና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የምታከናውናቸውን ተግባራት ለመደገፍ የሚደረጉ ድጋፎች ይጠናከራሉም ነው ያሉት፡፡