የሀገር ውስጥ ዜና

በጦርነት የተጎዱ ዜጎችን መልሶ በማቋቋም ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መረባረብ እንደሚገባ ተመለከተ

By ዮሐንስ ደርበው

March 31, 2023

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜኑ ጦርነት የተጎዱ ዜጎችን መልሶ በማቋቋም ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ።

የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመልሶ ግንባታ ዙሪያ በባህር ዳር እየመከረ ነው፡፡

በመድረኩ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ጀምበር (ዶ/ር)፣ የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የአማራ ክልል በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ገልፀዋል፡፡

አሁን ላይ በተደረሰው ስምምነት ጦርነቱን ማስቆም የተቻለ ቢሆንም ወደቀያቸው ያልተመለሱ በርካታ ነዋሪዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

የአማራ ክልል ወደ ተሟላና ዘላቂ ሰላም በመሸጋገር ዜጎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ለማድረግም በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጀት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ክሊዮፓስ ቶሮሪ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከጦርነቱ ማግስት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም ያለመ መርሐ ግብር እየተተገበረ ነው ብለዋል፡፡

መርሐ ግብሩ እንዲሳካ የመንግስት አካላት የማህበረሰብ መሪዎችና ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲረባረቡ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ከጦርነት ማግስት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና አካባቢው መልሶ እንዲቋቋም ለሚያደርገው ጥረት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ኮሚሽኑ በጦርነቱ ወቅት በሁሉም ወገኖች ትጥቅ ይዘው የተሳተፉ ዜጎችን ትጥቃቸውን በማስፈታት ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲገቡ አስፈላጊውን የመልሶ ማቋቋም ስራ እንደሚያከናውንም ነው የተናገሩት።

የመልሶ ማቋቋም ስራው ከፍተኛ ሀብት የሚጠይቅ በመሆኑ ደጋፊ አካላት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!