Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ቻይና እና ብራዚል የአሜሪካን ዶላር ከግብይታቸው ለማሥወጣት ተሥማሙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና እና ብራዚል የአሜሪካን ዶላር መጠቀም አቁመው በራሳቸው ምንዛሬ ለመገበያየት ስምምነት ላይ ደረሱ።

የብራዚል መንግስት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷ ሥምምነቱ በዓለም ሁለተኛዋ የትልቅ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችውን ቻይና እና በላቲን አሜሪካ የትልቅ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችውን ብራዚል ተጠቃሚ ያደርጋል ብሏል፡፡

በስምምነቱ መሰረት ሀገራቱ ግዙፍ የንግድ እና የገንዘብ ግብይታቸውን በቻይናው ገንዘብ “ዩዋን” እና በብራዚሉ የመገበያያ ገንዘብ “ሪአይስ” በቀጥታ የሚፈጽሙ ይሆናል፡፡

የብራዚል የንግድ እና ኢንቨስትመንት ማሥፋፊያ ኤጀንሲ በመረጃው እንዳመላከተው÷ ውሳኔው የሀገራቱን አላስፈላጊ ወጪ የሚቀንስ እና የሁለትዮሽ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ የሚያሳድግ ነው፡፡

መተግበሩ ቁርጥ ነው የተባለለት ሥምምነት በዚህ ዓመት ጥር ወር ላይ ቻይና እና ብራዚል ከፍተኛ ደረጃ ያለው የንግድ መድረክ ቤጂንግ ላይ ካካሄዱ በኋላ ይፋ መሆኑን ሲጂቲ ኤን ዘግቧል፡፡

በቻይናው “ዩዋን” እና በብራዚሉ መገበያያ ገንዘብ “ሪአይስ” የሚካሄደውን የሀገራቱን ግብይት የቻይናው “የኢንዱስትሪ እና ንግድ ባንክ” እንዲሁም የብራዚሉ “ኮሙኒኬሽን ባንክ”ያሳልጡታል ተብሏል፡፡

ቻይና ተመሳሳይ የንግድ ልውውጥ ሥምምነት ከሩሲያ፣ ፓኪስታን እና ሌሎች በርካታ ሀገራት ጋር ማድረጓን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

Exit mobile version