አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሸኔን በሚመለከት ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ከ10 በላይ ንግግሮች ተደርገዋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡
ቡድኑ አንድ የተሰባሰበ ኃይል ባለመሆኑ በሚደረጉ ንግግሮች የተለያዩ አካላት የተለያዩ ሃሳቦች ይዘው መቅረባቸው ጥረቶች ውጤት እንዳያመጡ እንቅፋት ሆኗል ብለዋል፡፡
“የኦሮሚያ ክልል ለሸኔ ያቀረበው የሰላም ጥሪ ክልሉ ያቀረበው ሳይሆን እንደ ፓርቲ ተነጋግረን የተወሰነ እና በምክትል ፕሬዚዳንት የሚመራ ኮሚቴ አቋቁመን ወደ ሥራ የተገባበትን የዚያን ተቀጥያ ነው የኦሮሚያ ክልል ያብራራው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ብዙ ሰው እየተጎዳ በመሆኑ ሰላሙን የሚጠላ ሰው ይኖራል ብዬ አላስብም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ችግሩ በሰላም እንዲፈታ አበክረን እንሰራለን በማለትም አብራርተዋል፡፡
ለሰላም መስፈኑ እየተሰራ ባለበት ወቅትም ተጨማሪ ግድያና ማፈናቀል እንዳይከሰት የጸጥታ ኃይሎች አስፈላጊውን ደህንነት የማስጠበቅ ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ለሰላም በሚደረገው ጥረት ዙሪያ ማንም ጥርጣሬ ሊገባው አይገባም በማለት ሸኔን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የታጣቁ ሃይሎች መንግስት የሚፈልገው ጉዳዩን በንግግር መፍታት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“መገዳደል አይጠቅምም የሚል የፀና አቋም አለን” ያሉ ሲሆን፥ የሚጠቅመውም ንግግር ብቻ ነው በማለት አብራርተዋል፡፡
ከዚህም አኳያ የሸኔ ጉዳይ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ እንደሚገኝ እና ውጤቱንም በጋራ የምናየው ይሆናል ብለዋል፡፡
በታምራት በሻው