አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቋል፡፡
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን ጨምሮ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች፣ አታሼዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።
የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያ ዘመናዊ ሰራዊት ለመገንባት ከውጭ የምታስገባቸውን ቴክኖሎጂዎች በሀገር ውስጥ ለመተካት የጀመረው ጥረት በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አሳስበዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚገጥሙ ፈተናዎችን በብቃት እያለፈ እንደሚገኝና ለዚህም እንደ የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ አይነት የትምህርት ተቋማት ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኮማንዳንት ብርጋዴር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ በበኩላቸው÷ ዩኒቨርሲቲው ከ75 በላይ መደበኛ መርሐ ግብሮች እንዳሉት ተናግረዋል፡፡
ተመራቂዎች በምህንድስና እና በጤና ዘርፍ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው ተብሏል።
በዕለቱ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ከሚመረቁት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊቱ አባላት በተጨማሪ ሲቪሎችና የጎረቤት ሀገር ወታደሮች መሆናቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
በምርቃታ መርሐ-ግብሩ ላይ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎችም ሽልማት ተበርክቷል።