አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዳያስፖራው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ እንስቶ እስከ አሁን ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ።
በኢትዮጵያውያን ገንዘብና ጉልበት ብቻ እየተገነባ የሚገኘው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በመጋቢት ወር 2003 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ መቀመጡ የሚታወስ ነው፡፡
በተለያዩ የዓለም ሀገራት ከሦስት ሚሊየን በላይ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት እንዳሉ ይገለፃል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወንደወሰን ግርማ ለኢዜአ እንገለጹት ፥ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ ስኬታማነት በጉልበት፣ በገንዘብና በሃሳብ ድጋፍ እያደረጉ ነው።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባሉ 12 ዓመታት ውስጥ ከ50 ሚሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ነው የገለጹት።
ከገንዘብ ድጋፉ ውጪ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት የሕዳሴ ግድብን ግንባታ ለማስተጓጎል የሚሞክሩ የውጭ ኃይሎችን እንቅስቃሴ በአደባባይ በመቃወም እውነታውን ለዓለም በማሳወቅ ረገድ የማይተካ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡