የሀገር ውስጥ ዜና

የአዋጁን ድንጋጌዎች ለዜጎች ጥቅምና ለሃገር ደህንነት ሲባል ሁሉም ተግባራዊ ማድረግ ይገባዋል – አቶ ደመቀ መኮንን

By Tibebu Kebede

April 13, 2020

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዝርዝር ድንጋጌዎችን ለዜጎች ጥቅምና ለሃገር ደህንነት ሲባል እያንዳንዱ ዜጋ ተግባራዊ ሊያደርግ እንደሚገባው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የታወጀውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸምን በበላይነት የሚመራው የሚኒስትሮች ኮሚቴ አስተባባሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኮሚቴው አባላት ሚኒስትሮችና ከሕግ አስከባሪ አካላት ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።

አቶ ደመቀ በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ የኮቪድ19 ወረርሽኝ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን አስታውሰው፥ ወረርሽኙን በጊዜ መቆጣጠር ካልተቻለ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ብለዋል።

የሃገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስና የደህንነት አባላት ራሳቸውን ከቫይረሱ ከመጠበቅና የሃገር ሉዓላዊነትን ከማስጠበቅ አልፈው ማህበረሰቡን ለመታደግ ትልቅ ተልዕኮ መሸከማቸውን አቶ ደመቀ አንስተዋል።

አዋጁን ተፈጻሚ ለማድረግ እስከታችኛው መዋቅር አደረጃጀት እንደሚያስፈልግ ያነሱት አቶ ደመቀ፥ በቀጣይ ሁሉም ሥራውን ተከፋፍሎ የሚሰራበት አካሄድ እንደሚኖር አመላክተዋል።

በአሰራሩ ኮሚቴው በየዕለቱ በቪዲዮ ኮንፈረስ በመገናኘት የመረጃ ልውውጥ የሚያደርግ ሲሆን፥ የሚያስፈልጉ የድጋፍ ሥራዎችንም ያከናውናል ተብሏል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በአዋጁ አፈጻጸም ደንብ፣ ይዘትና አተገባበር ላይ ሃሳቦች አቅርበው ምላሽ እንደተሰጠባቸው ኢዜአ ዘግቧል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ! https://t.me/fanatelevision