አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ካለፉት ዘጠኝ ዓመታት ወዲህ ከዘር አመራረት እና ግብይት ጋር የተያያዙ አራት ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየተገበረ መሆኑን ገለጸ፡፡
ፕሮጀክቶቹም የቀጥታ የዘር ግብይት ስርዓት፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አቀፍ ዘር ብዜት፣ የግብርና ግብዓት አቅርቦትና አገልግሎት ማዕከል እና የኢትዮጵያ የዘር ስርዓት ተቋማዊ ድጋፍ ናቸው፡፡
የቀጥታ የዘር ግብይት ስርዓቱ÷ ዘር አምራቾች የራሳቸውን ወኪሎች በመጠቀም የዘር አቅርቦትን ለአርሶ አደሮች የሚያደርሱበትን አሰራር መፍጠር ብሎም ለአርሶ አደሩ ጥራቱ የተመሰከረለት ዘር በወቅቱ፣ በሚፈለገው መጠንና የዝርያ ዓይነት እንዲቀርብ ለማስቻል ያለመ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ በ2002 ዓ.ም በሁለት ወረዳዎች ተጀምሮ በ2012/13 ዓ.ም በ320 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ መደረጉን በኢንስቲትዩቱ የኢትዮጵያ የዘር ስርዓት ተቋማት የፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ይትባረክ ሰምአነ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
ለአሰራሩ የማስፈፀሚያ መመሪያ ተቀርፆ በመደበኛ አሰራር እየተተገበረ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የኅብረት ሥራ ማኅበራት አቀፍ ዘር ብዜት ፕሮጀክት ዓላማ÷ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና ዩኒየኖች ዘር በማምረትና ግብይት ተግባር ውስጥ እንዲገቡና በዘላቂነት እንዲቀጥሉ ማገዝ መሆኑንም አስተባባሪው ጠቁመዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በአራት ክልሎች 14 ማኅበራትን ያቋቋመ ሲሆን÷ ማኅበራቱም በትግራይ 52 በመቶ፣ በደቡብ 30 በመቶ፣ በአማራ 20 በመቶ እና በኦሮሚያ 10 በመቶ የክልሉን የምርጥ ዘር ፍላጎት ማሟላት ችለዋል ነው ያሉት፡፡
ከፈረንጆቹ 2022 ጀምሮ የግልና የኅብረት ስራ ማኅበራት አቀፍ የዘር ብዜት ፕሮጀክት ተቀርፆ እየተተገበረ ነውም ብለዋል፡፡
የግብርና ግብዓት አቅርቦት እና አገልግሎት ማዕከላት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ማዕከላቱን 300 በሚሆኑ የግብርና ኮሜርሺያላይዜሽን የወረዳዎች የማቋቋም፣ ተሞክሮዎችንም የማስፋፋትና የመተግበር ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ዓላማ ሁሉም የግብርና ግብዓቶችን (ዘር፣ አግሮ ኬሚካል፣ የእንስሳት ህክምና መድሃኒት፣ መኖ፣ የእርሻ መሳሪያዎች) በሁሉም ግብዓት ሙያዊ ምክርን መሰረት ባደረገ መልኩ በጥራት፣ በሚፈለገው መጠን፣ ጊዜ እና በተመጣጣኝ ዋጋ በአንድ ማዕከል ለተጠቃሚው ተደራሽ ማድረግ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ እና ደቡብ ክልሎች 201 ማዕከላት ተቋቁመው 3 ነጥብ 8 ሚሊየን አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን የጠቀሱት አስተባባሪው፥ በያዝነው ዓመት ተጨማሪ ማዕከላትን ከ50 ለማያንሱ ወረዳዎች ለመገንባት ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል።
ለአሰራሩም የማስፈፀሚያ መመሪያ ፀድቆ በመደበኛ አሰራር እንዲተገበር ጥረት እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በዮሐንስ ደርበው
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!