የሀገር ውስጥ ዜና

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ ከዩ ኤስ ኤድ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ  

By Shambel Mihret

March 13, 2023

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤድ) የሥራ ኃላፊዎች ጋር በግብርናው ዘርፍ ላይ በትብብር ለመስራት ተወያዩ፡፡

 

ሚኒስትሩ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት÷ ሚኒስቴሩ ግብርናውን ለማዘመን የ10 ዓመት እስትራቴጂ ሠነድ ቀርጾ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል፡፡

 

በዚህም በበጋ ስንዴ ልማት፣ በአረንጓዴ ዐሻራና መሰል ሥራዎች አበረታች ለውጦች ተገኝተዋል ብለዋል፡፡

 

ዩ ኤስ ኤድ ከግብርናው ባሻገር እንደ ሀገር ትልቅ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

 

የዩ ኤስ ኤድ የሥራ ኃላፊ ሲን ጆንስ በበኩላቸው÷ በአሁኑ ወቅት እንደሀገር በግብርናው ዘርፍ በተለይ በስንዴ ልማት ላይ እየተሰራ ያለውን ስራ ማድነቃቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

 

በቀጣይም በምርጥ ዘር አቅርቦት፣ በመካናይዜሽን ማሽኖች ጥገና እና መለዋወጫ ዕቃዎችን በማቅረብ በተለይ እነዚህ አገልግሎቶች በማይገኙባቸው ገጠራማ አካባቢዎች ተደራሽ የማድረግ ስራን እንሰራለን ነው ያሉት፡፡