Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በጎንደር ከተማ እና በዙሪያዋ በቡድን የተደራጅተው ህገ ወጥ ተግባር ሲፈፅሙ የነበሩ 77 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 3 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ)በጎንደር ከተማ እና በዙሪያዋ ባሉ ወረዳዎች በቡድን የተደራጅተው ህገ ወጥ ተግባር ሲፈፅሙ የነበሩ 77 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የከተማዋ ፀጥታ ምክር ቤት አስታወቀ።

በከተማዋ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሠላም መደፍረስ፣ ሕገ-ወጥነትና አለመረጋጋት እየተስዋለ እንደነበር ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

ይህም የከተማዋ ህዝብ የፈለገውን ሠላምና ልማት በተገቢው መንገድ እንዳያገኝ ማድረጉ ነው የተነገረው።

መንግስትም የህገ ወጥ ተግባራን ለማስወገድ በሕገ ወጥ ዘራፊ ቡድን ተደራጅቶና ከነብስወከፍ እስከ ቡድን መሣሪያ ታጥቆ በካምፕ ሆኖ በርካታ ሕገ-ወጥ ድርጊት ሲፈፅም ከነበረው ኃይል ጋር ችግሩን በሕጋዊና በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ሲሞክር ነበረ ተብሏል።

ሆኖም ሕገ-ወጥ ተግባራት ተጠናክረው በመቀጠላቸው እና በፀጥታ ኃይሎች ላይ በተፈፀመ ጥቃት መንግስት እርምጃ መውሰዱ ነው የተነገረው።

በሕገ-ወጥ ቡድኑ ላይ በተወሰደው እርምጃ በከተማ መሬት ዝርፊያ፣ በሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ በዝርፊያና በቅሚያ ተሰማርቶ የነበሩ ግለሰቦች ከዚህ ተግባር መቆጠባቸውን ከአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የከተማዋ ፀጥታ ምክር ቤት ከዚህ በኋላ ለሕዝብ ሥጋት የሆነና መንግሥትን የሚገዳደር የታጠቀና የተደራጀ ቡድን እንደማይኖር ነው ያስታወቀው፡፡

Exit mobile version