የሀገር ውስጥ ዜና

ከሶማሊያ ተፈናቅለው ወደ ኢትዮጵያ ለገቡ 100 ሺህ ያህል ሥደተኞች ዕርዳታ እየደረሰ ነው – የተመድ የሥደተኞች ኤጀንሲ

By Alemayehu Geremew

March 07, 2023

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በግጭት ምክንያት በቅርቡ ከሶማሊያ ተፈናቅለው ወደ ኢትዮጵያ ለገቡ 100 ሺህ ያህል ሥደተኞች ዕርዳታ እየደረሰ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ሥደተኞቹ ባለፉት አራት ሣምንታት ውስጥ ከግጭት ቀጣናው ተሰደው ወደ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን የገቡ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ የገቡይ ሥደተኞች ምግብ ፣ የዓልሚ ምግብ ፣ የመጠጥ ውሃ ፣ የመጠለያ እና የሕክምና ቁሳቁስ አቅርቦት እንደሚያስፈልጋቸው መናገራቸውን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ከሥደተኞቹ አብዛኛዎቹ እናቶች ፣ ሕፃናት እና አዛውንቶች መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡

ምንም እንኳን የኢትዮጵያ መንግስት በአካባቢው ውስን የመጠለያ ፣ የጤና ኬላ እና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ቢኖረውም ለሥደተኞቹ ግን በሩን ክፍት ማድረጉን ኤጀንሲው ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የሥደተኞች እና ከሥደት ተመላሾች አገልግሎት ከተመዱ የሥደተኞች ኤጀንሲ ፣ ከሌሎች ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ አጋር አካላት ጋር በመሆን ስደተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ መግባት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ እያቀረቡ መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡