አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮና ቫይረስን ለመቆጣጠር ለሚደረገው ጥረት ከ17 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ተጠሪ ተቋማትና አምራች ኢንዱስትሪዎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት በመደገፍ ነው የ17 ሚሊየን 7 ሺህ 265 ብር የገንዘብ ድጋፉን ያደረጉት።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አለበል መላኩ ድጋፉ ለብሔራዊ ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ በተሰጠበት ወቅት ጊዜው ቀለብና ጥሪት የምንሰበስብበት ሳይሆን ራሳችንን አትርፈን ሌሎችን የምናተርፍበት ጊዜ መሆኑን ገልፀዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም የተፈጠረውን መጥፎ አጋጣሚ በመጠቀም ለመለገስ ሳይሆን በወገኖቻቸው ስቃይና ሞት ለመክበር የሚሹ አንዳንድ አምራች፣ የኢንዱስትሪ ባለቤቶችና ነጋዴዎች እየሰሩት ያለው ስራ አስነዋሪና ጊዜ የማይሽረው ሀገርና ህዝብ የማይረሳው መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም መጥፎ ታሪክን ከመስራት ተቆጥበው ከህዝብና መንግስት ጎን በመቆም ቫይረሱን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሀገራዊና ሰብዓዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የሚደረገው ድጋፍም ቫይረሱ በቁጥጥር ስር እስከሚውል ድረስ እንደሚቀጥል መገለፁን ከንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።