ቴክ

ቻይና “በጣም አስፈላጊ” በሆኑ የቴክኖሎጅ ግኝቶች በቀዳሚነት እየመራች መሆኑ ተገለጸ

By Alemayehu Geremew

March 03, 2023

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና በደኅንነቱ ዘርፍ እያቆጠቆጡ በመጡ እና “በጣም አስፈላጊ” በሆኑ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ዓለማችንን እየመራች መሆኑ ተገለጸ፡፡

የአውስትራሊያ ስትራቴጂያዊ ፖሊሲ ኢኒስቲትዩት ይፋ ባደረገው ጥናት እንዳመላከተው አሁን ላይ 44 የሣይንስና ቴክኖሎጂ ግኝቶች እያቆጠቆጡ ነው።

ከዚህ ውስጥ ቻይና በ37ቱ ወሳኝ የሣይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች ቀዳሚውን ሥፍራ ይዛለች ነው ያለው፡፡

ቻይና የቀዳሚነት ሥፍራውን የተቆናጠጠችው በመከላከያ ፣ በጠፈር ምርምር ፣ በሮቦቲክስ ፣ በኃይል ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ ባዮ-ቴክኖሎጂ ፣ሰው ሠራሽ አስተውኅሎት እንዲሁም በኳንተም ቴክኖሎጂ እና በረቀቁ ቁሶች ላይ በሠራቻቸው እና ባበረከተቻቸው የሣይንስና ቴክኖሎጂ ግኝቶች መሆኑም ኢኒስቲትዩቱ በዝርዝር አመላክቷል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም ቤጂንግ አሁን ላይ ራሷን የዓለማችን የሣይንስና ቴክኖሎጂ ልዕለ ኃያል ሀገር ማድረግ መቻሏን አር ቲ በዘገባው አመላክቷል።

ጥናቱ እንዳመላከተው ዓለም ላይ ምርጥ የሚባሉት 10 የምርምር ተቋማት በቻይና ይገኛሉ።

እንዲያውም ቻይና ነሐሤ 2021 ላይ ይፋ ያደረገቻቸው የኒውክሌር አረር የመሸከም ዐቅም ያላቸው ኃይፐር ሶኒክ ሚሳኤሎቿ አሜሪካን ማስገረሙንም ነው ኢኒስቲትዩት የገለጸው፡፡

ባለፉት አምስት አመታት ቻይና ዓለም ላይ የቀረቡና ከፍተኛ ተፅዕኖ ያላቸውን 48 ነጥብ 49 በመቶ የጥናት ውጤቶች ተጠቅማ ዘመናዊ የአውሮፕላን ሞተር መስራቷን ኢንስቲቲዩቱ አመላክቷል።