አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 2 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ተጨማሪ ዘጠኝ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው አስታወቀ።
ባለፉት 24 ሰዓታት የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 442 ሰዎች መካከል ዘጠኙ የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው መረጋገጡን አስታውቋል።
ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 65 ከፍ ማለቱን ኢዜአ ዘግቧል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደተናገሩት ዛሬ ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጠው ሁሉም ግለሰቦች የጉዞ ታሪክ ያላቸው ናቸው።
ከግለሰቦቹ መካከል ሰባቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ አንድ ኤርትራዊ ቀሪዋ ደግሞ የህንድ ዜግነት ያላት መሆኗንም ተናግረዋል።
አራቱ ኢትዮጵያውያን ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በለይቶ ማቆያ ክትትል ሲያደርጉ የነበሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሁለቱ የቱርክ እንዲሁም ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ደግሞ የእንግሊዝ ሃገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው ሲሆን ሁሉም በለይቶ ማቆያ ውስጥ ክትትል ሲያደርጉ መቆየታቸውን አውስተዋል።
የ20 ዓመቷ ህንዳዊት የአሜሪካ እንዲሁም የ40 ዓመቱ ኤርትራዊ ደግሞ የዱባይ ጉዞ ታሪክ ያላት ናቸው ብለዋል።
በጽኑ ሕሙማን ክፍል ከሚገኙት ሁለት ግለሰቦች መካከል አንዱ የጤና መሻሻል በማሳየቱ ከክፍሉ መውጣቱንም ዶክተር ሊያ አስረድተዋል።
እስካሁን ባለው ሂደትም በኢትዮጵያ ለ3 ሺህ 232 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ መደረጉን ጠቁመው፥ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 57ቱ የሕክምና ክትትል እያደረጉ ይገኛሉም ነው ያሉት።
አራት ግለሰቦች ከቫይረሱ ያገገሙ ሲሆን ሁለቱ በቫይረሱ ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።
ሌሎች ሁለት ግለሰቦች ደግሞ ወደ ሃገራቸው ተሸኝተዋል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ! https://t.me/fanatelevision